በምዕራብ ወለጋ የመኽር ሰብል ሙሉ ለሙሉ ተሰበሰበ

1843

ነቀምቴ፣ ጥር 07/2013 /ኢዜአ/ በምዕራብ ወለጋ ዞን በ273 ሺህ 164 ሄክታር መሬት ላይ የለማ የመኽር ሰብል ሙሉ በሙሉ መሰብሰቡን የዞኑ የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ኅላፊ አቶ አብርሃም ደሜ ለኢዜአ እንደገለጹት በዞኑ በ2012/2013 ምርት ዘመን የመኽር ወቅት ሰብል ሙሉ ለሙሉ ተሰብስቧል።

ከተሰበሰበው ሰብል 10 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ አመላክተዋል።

በሰብል ስብሰባ ወቅት የምርት ብክነት እንዳያጋጥም ለአርሶ አደሩ የሙያ ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል።

“የምርት ብክነት ከሚያስከትሉ አንዱ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ነው” ያሉት ስራ አሰኪያጁ በዚህ ዓመት ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ሳይከሰት ሰብሉ ተሰብስቦ መጠናቀቁ ለአርሶ አደሩ ጥሩ አጋጣሚ የፈጠረ መሆኑን አስታውቀዋል።

የዞኑ አርሶ አደሮች በበኩላቸው የነበረውን አመቺ የአየር ሁኔታ በመጠቀም ሰብላቸውን ሰብሰበው  ማጠናቀቃቸውን ተናግረዋል።

በዞኑ ሆማ ወረዳ ቀበሌ 01  ነዋሪ አርሶ አደር ግዛው ደምሴ እንደገለጹት በሶስት ሄክታር ማሳቸው ላይ ያለሙትን የበቆሎ ሰብል ሙሉ ለሙሉ ሰብስበዋል።

“የነበረው አመቺ የአየር ሁኔታ የምርት ብክነትን በመቀነስ ሰብል ሰብስቤ እንዳጠናቅቅ ረድቶኛል” ብለዋል።

“በዚህ ዓመት ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ባለመዝነቡ ለምርት ስብሰባ አመቺ ሁኔታ ፈጥሮልናል” ያሉት ደግሞ የቀበሌው ነዋሪ አርሶ አደር አሊ ናዶ ናቸው ።

በምርት ወቀቱ በ2 ነጥብ 5 ሄክታር  ማሳቸው ላይ ያለሙትን በቆሎ በደቦና በቤተሰብ አባላት ጉልበት በመታገዝ መሰብሰባቸውን አስታውቀዋል ።