የደቡብ ክልል ምክር ቤት ጉባኤ ሹመት በመስጠት፣ ተጨማሪ በጀትና አዋጅ በማጽደቅ ተጠናቀቀ

129

ሀዋሳ፣ ጥር 7/2013( ኢዜአ) የደቡብ ክልል ምክር ቤት ለሰባት ቢሮ ኅላፊዎች ሹመት በመስጠት እንዲሁም ከ616 ሚሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ በጀትና አዋጆችን በማጽደቅ ተጠናቀቀ። 

ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 5ኛ ዙር 6ኛ ዓመት 3ኛ አስቸኳይ ጉባኤ በውክልና ሲሰሩ የቆዩ ሰባት የቢሮ ኅላፊዎች፣ የክልሉ ኦዲት ቢሮ ዋናና ምክትል ኦዲተሮችን እንዲሁም የስድስት ዳኞችን ሹመት አጽድቋል።

በዚህ መሰረት አቶ ተስፋዬ ይገዙ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኅላፊ፣ አቶ አንተነህ ፈቃዱ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ  የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኅላፊ፣ አቶ ሀይለማርያም ተስፋዬ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ  የባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ኅላፊ በመሆን ተሹመዋል።

በተጨማሪም አቶ አክሊሉ አዳኝ የውሀ መስኖና ኢነርጂ ቢሮ ኅላፊ፣ አቶ ተሾመ ታከለ የኢንተርፕራይዞችና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኅላፊ፣ አቶ ገብሬ ናቄ የሳይንስ፣ ኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ኅላፊ፣ አቶ ማሄ ቦዳ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኅላፊ በመሆን ተሹመዋል።

እንዲሁም ወይዘሮ ፈዲላ አደም የደቡብ ክልል ኦዲት ቢሮ ዋና ኦዲተር፣ አቶ በላይነህ ሀቹላ ምክትል ዋና ኦዲተር በመሆን ተሹመዋል።

 በጎፋ ዞን ለሚገኙ ስድስት የመጀመሪያ ደረጃ የከተማና የወረዳ ፍርድ ቤቶች ዳኞች ተሹመዋል።

አስቸኳይ ጉባኤው የዞንና ክልል ምክር ቤት አባላትን ቁጥር ለመደንገግ የወጣውን አዋጅም አፅድቋል።

ምክር ቤቱ በክልሉ ኮሮናን ለመከላከል ለሚሰሩ ስራዎችና ለሌሎች ተግባራት ማስፈጸሚያ የሚሆን 616 ሚሊዮን 843 ሺህ 300 ብር ተጨማሪ በጀትም በማጽደቅ አስቸካይ ጉባኤውን አጠናቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም