ቢሮው በአዲስ አበባ ለሚገኙ 20 አካል ጉዳተኞች ዊልቼር አበረከተ - ኢዜአ አማርኛ
ቢሮው በአዲስ አበባ ለሚገኙ 20 አካል ጉዳተኞች ዊልቼር አበረከተ
አዲስ አበባ፣ ጥር 7/2013 ( ኢዜአ) የአዲስ አበባ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ከአጋፔ ሞቢሊቲ ኢትዮጵያ ያገኛቸውን 20 ዊልቼሮች ከሁሉም ክፍለ ከተሞች ለተውጣጡ አካል ጉዳተኞች አስረከበ።
ዊልቼሮቹ በአሜሪካ ከሚገኝውና በአካል ጉዳተኞች ድጋፍ ላይ ከሚሰራው አጋፔ ሞቢሊቲ ኢትዮጵያ ከተሰኘ ግብረ-ሠናይ ድርጅት ነው የተገኙት።
የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ አበባ እሸቴ የአካል ጉዳት ያለባቸውን ዜጎች እንደ ጉዳታቸው አይነት ድጋፍ ማድረግ እንዲቻል ከሁሉም ክፍለ ከተሞች መረጃ እየተሰበሰበ መሆኑን ገልፀዋል።
ለአካል ጉዳተኞቹ የተበረከቱትን ዊልቼሮች ቢሮው ከግብረ ሰናይ ድርጅቱ ጋር በመጻጻፍ ያገኛቸው እንደሆኑም ገልፀዋል።
የግብረ ሰናይ ድርጅቱ መስራችና ተወካይ ወይዘሮ ሳባ ተክለቂርቆስ ድጋፉ በድርጅቱ ስም በአሜሪካና በአውሮፓ ነዋሪ ከሆኑ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን መገኘቱን ተናግረዋል።
እርዳታው አካል ጉዳተኞች በጉዳታቸው ልክ ተደራሽ የሚያደርግ ሲሆን የመግዛት አቅም የሌላቸውን ችግረኞች፣ ወጣቶችንና እናቶችን መሠረት አድርጎም ድጋፉ እንዲደርሳቸው መደረጉን አስረድተዋል።