የእናቶች ማቆያ ያላቸው ጤና ጣቢያዎች 60 በመቶ ደርሰዋል

150

አዲስ አበባ፣ ጥር 7/2013 ( ኢዜአ) በኢትዮጵያ የእናቶች ማቆያ ያላቸው ጤና ጣቢያዎች 60 በመቶ መድረሱን ጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

በኢትዮጵያ ለ15ኛ ጊዜ እየተከበረ የሚገኘው የጤናማ እናትነት ወር በወሊድ ወቅት የሚከሰትን የእናቶች ሞት ለመቀነስ ግንዛቤ በሚያሳድጉ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው።

በሚኒስቴሩ የእናቶች ጤና ቡድን አስተባባሪ አቶ ዘነበ አካሌ ለኢዜአ እንዳሉት በኢትዮጵያ ከወሊድ በኋላ በሚከሰት የደም መፍሰስ 50 በመቶዎቹ እናቶች ሕይወታቸውን ያጣሉ።

የእናቶች አገልግሎት ፈልገው ወደ ጤና ተቋም አለመምጣት ቀዳሚው ቢሆንም፤ ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት አለማግኘትና የመንገድ መሰረተ ልማት ችግሮች በወሊድ ጊዜ ለሚከሰተው ሞት ምክንያቶች ናቸው።

በእነዚህና ሌሎችም ምክንያቶች 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን እናቶች በቤት ውስጥ ይወልዳሉ ነው ያሉት አቶ ዘነበ።

አንዲት እናት ከወለደች በኋላ በሚያጋጥማት የደም መፍሰስ ሁለት ሠዓት ባልሞላ ጊዜ ሕይወቷን እንደምታጣ ገልፀው በኢትዮጵያም በርካታ እናቶች ከወለዱ በኋላ በሚከሰት የደም መፍሰስ ህይወታቸውን የሚያጡ መሆኑን ተናግረዋል።

በወቅቱ ወደ ሕክምና ተቋም እንዲመጡ ግንዛቤ ማስፋት፣ ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት መስጠትና መሰረተ ልማት ማሟላትን ለችግሩ በመፍትሄነት አስቀምጠዋል።

ጤና ሚኒስቴር በተለይም ከጤና ተቋም ርቀት ባላቸው አካባቢዎች የሚኖሩ እናቶች የመውለጃ ቀናቸው ሲቃረብ የሚቆዩባቸውን ቦታዎች ማዘጋጀትን አንደኛው መፍትሄ አድርጎ ሲሰራ መቆየቱን አስረድተዋል።

በዚህም በአገሪቷ የእናቶች ማቆያ ያላቸው ጤና ጣቢያዎች 60 በመቶ መድረሱን ተናግረዋል።

እንደ አስተባባሪው ገለጻ ማቆያው በየቀኑ በወሊድ ምክንያት ሕይወታቸውን እያጡ ያሉትን 30 እናቶች ወደ አምስት ለመቀነስ እየተሰራ ላለው ስራ እገዛ ያደርጋል።

ማቆያው እናቶች በቤት ውስጥ ለመውለድ በሚያደርጉት ሙከራ በሚከሰት የተራዘመ ምጥ የሚሞቱ እናቶችን ሕይወት ለመታደግ ያለውን ፋይዳም አብራርተዋል።  

በሌላ በኩል የእናቶችን ሞት ለመቀነስ 30 በመቶ አስተዋጽኦ የሚያደርገውን የቤተሰብ ዕቅድ ተደራሽ ማድረግ በቀጣይ በትኩረት የሚሰራበት እንደሆነ ገልፀዋል።

የቤተሰብ ዕቅድ አንዲት እናት እርግዝናዋ በፈለገችበት ወቅት እንዲከሰት ስለሚያደርግ ለልጇና ለራሷም ጤንነት በወቅቱ ወደ ጤና ተቋም እንድትሄድ አስተዋጽኦ አለው።

በኢትዮጵያ ከሚወልዱ መቶ ሺህ እናቶች መካከል 401ዱ በወሊድ ምክንያት ሕይወታቸውን የሚያጡ ሲሆን  በቀጣዮቹ 10 ዓመታት አሃዙን ወደ 140 ዝቅ ለማድረግ ታቅዷል ብለዋል።

ባለፉት 15 ዓመታት ከወሊድ ጋር በተገናኘ ሕይወታቸውን የሚያጡ እናቶችን ሞት ለመቀነስ በተከናወነ ተግባር 72 በመቶ መቀነስ እንደተቻለ የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።

የጤናማ እናትነት ወር መርሃ ግብር እስከ ጥር 30 በተለያዩ ዝግጅቶች የሚቀጥል ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም