በሀዋሳ ከተማ ከሁለት ቢሊዮን 400 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሀብቶች ወደ ስራ ገቡ

1722

ሐዋሳ፣ ጥር 07/2013 (ኢዜአ) በሐዋሳ ከተማ ባለፉት ስድስት ወራት ከሁለት ቢሊዮን 400 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 22 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው ወደ ሥራ መግባታቸውን የከተማዋ አስተዳደር አስታወቀ።

በከተማዋ ያለውን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴና በመስኩ ያጋጠሙ ችግሮችን የሚገመግም የምክክር መድረክ በሀዋሳ ተካሂዷል።

በምክክር መድረኩ የከተማዋ አስተዳደር የኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ በላይነህ ተሾመ እንዳሉት ባለሀብቶቹ ወደ ሥራ የገቡባቸው መስኮች ግብርና፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ አገልግሎትና ግንባታ ላይ ነው።

ከሁለት ቢሊዮን 400ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል በማስመዝገብ ወደ ስራ የገቡት ባለሀብቶቹ  ከ3 ሺህ ለሚበልጡ የከተማዋ ነዋሪዎች ጊዜያዊና ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን አስታውቀዋል።

በከተማዋ ያለው ሠላማዊ ሁኔታ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ብልጫ ያለው ባለሀብት ወደ ስራ ለማስገባት ማስቻሉን ጠቁመዋል።

በከተማዋ ያለውን የባለሀብቶች እንቅስቃሴ በመገምገም የኢንቨስትመንት ፈቃድ አውጥተው ቦታ በመረከብ ወደ ስራ ያልገቡ 120 ባለሀብቶች ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው ጠቁመዋል።

የተሰጣቸውን መሬት ሳያለሙ አጥረው በማስቀመጥ ለሌላ ያከራዩ መኖራቸውንም ጠቁመው በስድስት ወራት ውስጥ ወደ ስራ እንዲገቡ የጊዜ ገደብ እንደተቀመጠላቸው ገልጸዋል።

የሃዋሳ ከተማ አስተዳደር ምክትል ካንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ጸጋዬ ቱኬ በበኩላቸው አስተዳደሩ በተገቢው መንገድ ወደ ስራ የገቡ ባለሀብቶችን ለመደገፍ የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋቱን ተናግረዋል።

ባለሀብቱ በተሰጠው የአንቨስትመንት ፈቃድ መሰረት የተረከበውን ቦታ ለተገቢው ዓላማ በማዋል ለከተማዋ እድገት የሚጠበቅበትን ሀላፊነት እንዲወጣም አሳስበዋል።

ባለሀብቱ በስራው ላይ የሚያጋጥሙት ችግሮች ካሉ ለሚመለከተው አካል በማቅረብ መፍታት የሚቻል መሆኑን አስረድተዋል።

ከመድረኩ ተሳታፊ  ባለሀብቶች መካከል የአበባ ጨርቃ ጨርቅና ስፌት ፋብርካ ተወካይ አቶ ወሌ አበጋዝ በሰጡት አስተያየት በተሰማሩበት የኢንዱስትሪ መንደር አካባቢ መንገድ በተገቢው መንገድ ያልወጣለት በመሆኑ በስራቸው ላይ ጫና እንዳሳደረ ተናግረዋል።

የኤሌክትሪክ ሀይልን ጨምሮ  ሌሎች የመሰረተ ልማት አቅርቦት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን በፍጥነት መፍታት ተገቢ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩት አቶ አባተ ኪሾ  በበኩላቸው የከተማ አስተዳደሩ ባለሀብቱ ያለበትን ችግር ለመፍታት እያደረገ ያለው ጥረት የሚያስመሰግን መሆኑን ገልጸዋል።

መሬት ወስዶ አለማልማት ለባለሀብቱም ሆነ ለሀገር ጉዳት እንዳለው ጠቁመው  ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን የከተማ አስተዳደሩ ከባለሀብቶቹ ጋር በመሆን መፍታት አለበት ብለዋል።

በምክክር መድረኩ ከባለሀብቶችና ከተማዋ አስተዳደሩ ተቋማት የተውጣጡ 11 አባላት ያሉት የሀዋሳ ከተማ ልማት ምክር ቤት ተቋቁሟል።

ምክር ቤቱ የከተማዋን እድገት ለማፋጠንና ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እንደሚሰራ ተጠቁሟል።