የገበታ ለአገር ፕሮጀክቶችን የሚመጥን የመስተንግዶና የሆቴል ቱሪዝም አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የገበታ ለአገር ፕሮጀክቶችን የሚመጥን የመስተንግዶና የሆቴል ቱሪዝም አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 7/2013 ( ኢዜአ) በገበታ ለአገር የሚገነቡ ፕሮጀክቶችን የሚመጥን የመስተንግዶና የሆቴል ቱሪዝም አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የሆቴልና ቱሪዝም ሥራ ማሰልጠኛ ማዕከል አስታወቀ።
የኢትዮጵያን የቱሪስት መዳረሻነት ለማሳደግ እየተከናወኑ ከሚገኙ ተግባራት መካከል የገበታ ለአገር ፕሮጀክቶች ይጠቀሳሉ።
ፕሮጀክቶቹ በጎርጎራ፣ በወንጪና በኮይሻ አካባቢዎች የተፈጥሮ መስህቦችን መሰረት በማድረግ ዘመናዊና ማራኪ የቱሪዝም መዳረሻዎች የሚገነቡባቸው ናቸው።
ፕሮጀክቶቹ የአገሪቷን የቱሪዝም ዕድገት ከፍ የሚያደርጉ መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ፕሮጀክቶቹን ይፋ ባደረጉበት ጊዜ መግለጻቸው ይታወቃል።
የማዕከሉ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ አባተ ኢትዮጵያ ያልታዩና ጥቅም ላይ ያልዋሉ እምቅ የቱሪዝም ሃብቶች ያሏት አገር ብትሆንም በአግባቡ ባለመልማታቸው ከዘርፉ የሚፈለገውን ያህል ጥቅም እየተገኘ አይደለም ሲሉ ለኢዜአ ገልፀዋል።
'የገበታ ለአገር ፕሮጀክቶች አገሪቷ ያሏትን ተፈጥሯዊ መስህቦች ከማስተዋወቅ ባሻገር የቱሪዝም ሀብትን እንዴት ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚቻል ያሳዩ ናቸው' ብለዋል።
እነዚህ ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ የአገር ውስጡን ጨምሮ የውጭ አገራት ጎብኚዎች በብዛት ወደ ስፍራው ይመጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል።
ለዚህም ፕሮጀክቶቹን የሚመጥን ዘመናዊ የመስተንግዶና የሆቴል ቱሪዝም አገልግሎት እንዲኖር የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ነው የገለጹት።
በዝግጅት ምዕራፉ መስተንግዶው ኢትዮጵያዊ አኗኗር፣ አመጋገብ፣ አለባበስና ሌሎች ባሕሎችን የሚያስተዋውቅ እንዲሆን የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አቶ ገዛኸኝ ጠቁመዋል።
የገበያ ትስስርና የሥራ ዕድል ከመፍጠር አኳያ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር በሚያስችል መልኩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውንም አቶ ገዛኸኝ አክለዋል።
እንደ እርሳቸው ገለጻ በባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስተባባሪነት ከዘርፉ ተቋማትና ከክልሎች ጋር ቅንጅታዊ አሰራር ለማጠናከር ከወዲሁ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል።
"ፕሮጀክቶቹ በሚጎበኙባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ባሕላዊ እሴቶች ላይ በመመርኮዝ እስከታችኛው እርከን በጋራ የሚሰራበት አግባብ ይፈጠራል" ነው ያሉት አቶ ገዛኽኝ።
የሕዳሴ ግድብን ጨምሮ እየተገነቡ ያሉ የኃይል ማመንጫዎችም የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራ በዕቅድ ተይዞ እየተከናወነ መሆኑን አቶ ገዛኸኝ ጠቁመዋል።
ኃይል ማመንጫዎቹ ተጠናቀው ወደ ሥራ ሲገቡ የሚፈጠሩ ምቹ አጋጣሚዎችን ወደ ቱሪስት መዳረሻነት በመቀየር ዘርፈ ብዙ ጥቅም ማግኘት ይቻላል ነው ያሉት።