በመጪው አገራዊ ምርጫ የፀጥታና ደህንነት ችግር እንዳይኖር ዝግጅት እየተደረገ ነው

89

አዲስ አበባ፣ ጥር 7/2013 ( ኢዜአ) በዘንድሮው 6ኛ አገራዊ ምርጫ የፀጥታና ደህንነት ችግር እንዳያጋጥም ከወዲሁ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገለፀ።

ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በምርጫው ዕቅድ፣ አገራዊ የደህንነት ስጋቶች እንዲሁም የመፍትሄ አቅጣጫዎች ላይ ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ተወያይተዋል።

የምርጫውን ደህንነት ለማስጠበቅ በአገር አቀፍ ደረጃ የተቋቋመው ግብረሃይል ቀደም ሲል ባካሄደው ውይይት ክልሎች የየአካባቢያቸውን ችግሮች ለይተው የፀጥታ ዕቅድ እንዲያወጡ አቅጣጫ አስቀምጧል።

በዚሁ መሰረት ክልሎቹ ያወጡት ዝርዝር ዕቅድ ዛሬ ተገምግሞ ቀጣይ አቅጣጫ ተሰጥቶበታል።

የምርጫውን ደህንነት የሚፈታተኑ ችግሮችን ለይቶ ከፀጥታና ከሕግ አፈፃፀም አኳያ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ ላይ ያተኮረው ውይይት ምርጫውን ሠላማዊ ማድረግ በሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ መክሯል።

የምርጫ ዕቅድ ሪፖርት ካቀረቡ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች አዲስ አበባ፣ አማራ፣ ኦሮሚያና ሀረሪ ክልሎች የተሻለ ዕቅድ፣ ይዘትና ነባራዊ ሁኔታን ተንትኖ በማስቀመጥ ተሽለው ተገኝተዋል ተብሏል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ምርጫው ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲካሄድ ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

እያንዳንዱ ክልል ከፀጥታና ደህንነት አኳያ በተገቢው ትኩረት ችግሮችን ለይቶ መስራት አለበት ነው ያሉት።

ከዚህ አንፃር የምርጫውን ተሳታፊ አካላት መሰረት ያደረገ ዝርዝር ዕቅድ መውጣቱን ተናግረዋል።

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ በዕቅዱ የሁሉም ክልሎች ድክመትና ጥንካሬ መለየቱንና ዕቅዱ ምን ያህል ተጨባጭና ነባራዊ ሁኔታዎችን አይቷል የሚለው መገምገሙን ገልፀዋል።

በዕቅዱ መሰረት ክልሎች የምርጫ አፈፃፀሙን ሠላማዊ ማድረግ አለባቸው ያሉት ሰብሳቢዋ ከዚህ አንፃር ክፍተት ያለባቸው ችግሮቹን በቶሎ እንደሚያርሙ ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም