በመጠለያ ጣቢያዎች ለሚገኙ በተለይ የሴቶችና ህፃናትን ደህንነት ማስጠበቅ ትኩረት ያሻዋል- የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች

119

አዲስ አበባ፣ ጥር 7/2013 ( ኢዜአ) በመጠለያ ጣቢያዎች ለሚገኙ በተለይ የሴቶችና ህፃናትን ደህንነት ማስጠበቅ በመንግስት ልዩ ትኩረት እንዲደረግበት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጠየቀ።

ድርጅቶቹ በሀገሪቱ በተለያዩ ክልሎች በሰላም መደፍረስ ምክንያት ለተጎዱ ሴቶች፣ ህጻናትና አጠቃላይ ችግር ላይ ለሚገኙ  ዜጎች አስፈላጊው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቋል።

የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት ዳይሬክተር ወይዘሮ ሳባ ገብረመድህን፤ ግጭት በሚከሰትባቸው አካባቢዎች በተለይም የሴቶችና ህጻናት ችግርና እንግልት አሳሳቢ ሆኗል ብለዋል።

ችግር በሚፈጠርባቸው አካባቢዎች በሰላማዊ ዜጎች  ላይ እየደረሰ ያለው ግድያ፣ ዝርፊያ እንዲሁም የአስገድዶ መድፈር አሳሳቢ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በሰላም እጦት ሳቢያ ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ሴቶችና ህፃናት ደህንነት መንግስት ልዩ ትኩረት እንዲሰጥም ጠይቀዋል።

የተቋረጡ ማህበራዊ አገልግሎቶች እንዲመለሱ የምግብ፣ መድሃኒትና ሌሎች አቅርቦቶችም እንዲሟሉ የተጠናከረ ጥረት ሊደረግ ይገባል ብለዋል።

በዚህ ዙሪያ ችግሩን ለማቃለል መንግስት ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እና በጎ አድራጎት ተቋማት ጋር በቅርበትና በመተባበር መስራት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

ሰላማዊ ዜጎችን በመግደልና በማፈናቀል እየተሳተፉ ያሉ ወንጀለኞችን በማደን በቁጥጥር ስር ማዋልና የተጠናከረ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የአክሽን ኤይድ ኢትዮጵያ ዳይሬክተር ወይዘሮ ትነበብ ብርሀኔ በበኩላቸው ሀገር በቀል እና አለም አቀፍ ድጋፍ ሰጪዎች እንዲሁም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የምግብ፣ የውሀ፣ የህክምና እና ሌሎች ቁሳቁሶችን ድጋፍ በማድረግ ሁሉም እንዲረባረብ ጠይቀዋል።

ከመንግስት ጎን በመሆን ተጎጂዎችን መልሶ ለመቋቋም የሚደርገውን ጥረት የሲቪክ ማህበራት መደገፍ ይኖርባቸዋልም ነው ያሉት።

የሚዲያ ባለሙያዎች ግጭቶችና መፈናቀሎችን በተመለከተ የሚያቀርቡት ዘገባ የጋዜጠኝነትን ሙያዊ ስነ ምግባር ተከትሎ በወቅቱ ተደራሽ በመሆን ሰዎችን የሚታደግ እንዲሆንም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም