በጋምቤላ ክልል የመጠጥ ውሃ አገልግሎት ለማዳረስ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል-አቶ አሞድ ኡጁሉ

197

ጋምቤላ፣ ጥር 07/2013(ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል የመጠጥ ውሃ አገልግሎት በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አሞድ ኡጁሉ አስታወቁ።

ርዕሰ መስተዳድሩ የኢታንግ ከተማን የውሃ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ትናንት በመረቁበት ወቅት እንዳሉት በክልሉ ሰፊ የገጸና ከርሰ ምድር ውሃ ቢኖርም ህብረተሰቡ በሚፈለገው ልክ ተጠቃሚ ሳይሆን ቆይቷል።

የክልሉ መንግስት በከተማ ገጠር የንጹህ መጠጥ ውሃ  ተደራሽ የማድረጉ ተግባርን በማጠናክር  የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት  ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

በተለይም በቅርቡ በፌዴራል የውሃ ልማት ኮሚሽን ለሚጀመረው የጋምቤላ ከተማ ዘላቂ የንጹህ መጠጥ ውሃ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ስኬት የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ያደረጋል ብለዋል።

 በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የንጹህ መጠጥ ውሃ  ለማዳረስ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።

የክልሉ የውሃና መስኖ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ካን ጋልዋክ በበኩላቸው  በክልሉ  በአንድ ቋት የንጽህ መጠጥ ውሃና የሳንቴሽን ፕሮግራምና በአጋር ድርጅቶች ድጋፍ በሁሉም አካባቢዎች የንጹህ መጠጥ ውሃ ለማዳረስ  እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት በአንድ ቋት የንጹህ መጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን መርሃ ግብር የተመረቀውን የኢታንግ ከተማ የማስፋፊያ ፕሮጀክት ጨምሮ 67 የከተማና ገጠር የውሃ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት መብቃታቸውን አስታውቀዋል።

ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት ከጀመሩት ፕሮጀክቶች መካከል ስድስቱ የከተማ  ቀሪዎቹ የገጠር መለስተኛ እና  እጅ ውሃ ጉድጓዶች እንዲሁም የጎለበቱ ምንጮች እንደሆኑ ጠቅሰዋል።

ከ88 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነቡት እነዚሁ የውሃ ፕሮጀክቶች ከ47 ሺህ 380 በላይ ህዝብ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ማድረጋቸውን አቶ ካን ተናግረዋል።

በዕለቱ የተመረቀው የኢታንግ የውሃ ፕሮጀክት  አንድ ሺህ 63 ሜትር ኩብ ውሃ በቀን የማምረት አቅም እንዳለውና ከ13 ሺህ በላይ ህዝብ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተገልጿል።

በውሃ ፕሮጀክቱ ምረቃ ሥነ-ሥርዓት ከተገኙ የኢታንግ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ ጳውሎስ ኡቻን በሰጡት አስተያየት የውሃ ፕሮጀክቱ ቀደም ሲል በከተማው የነበረውን ከፍተኛ የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር  በማቃለሉ መደሰታቸውን ተናግረዋል።

ሌላዋ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ አፖና ኡጁሉ በበኩላቸው በአካባቢያቸው በነበረው የንጹህ መጠጥ ውሃ እጥረት ምክንያት ንጽህናው ያልተጠበቀው የባሮ ወንዝ ውሃን ሲጠቀሙ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

አሁን ግን የውሃ ተቋሙ  በመገንባቱ የንጹህ መጠጥ ውሃ አገልግሎት ተጠቃሚ እንደሆኑ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም