ኦነግ ሸኔ የኦሮሞ ህዝብ ጠላት ነው-የአንገር ጉቴ ከተማ ነዋሪዎች

1722

ነቀምቴ ፣ጥር 07/2013 /ኢዜአ/ የህወሀት ተላላኪ የሆነው ኦነግ ሸኔ የኦሮሞ ህዝበ ጠላት ነው ሲሉ በምሥራቅ ወለጋ ዞን በጊዳ አያና ወረዳ የአንገር ጉቴ ከተማ ነዋሪዎች አደባባይ በመውጣት በሰልፍ አወገዙ፡፡

በሺህ ዎች የሚቆጠሩ የከተማው ነዋሪዎች አደባባይ በመውጣት የኦነግ ሸኔ የኦሮሞ ሕዝብ ጠላት ነው፤ የኦኔግሸኔ የኦሮሞን ሕዝብ አይወክልም፤ የኦነግ ሸኔ የሕወሐት ተላላኪ ነው፤ የሚሉትን መፈክሮች በመያዝ ቡድኑን በሰልፍ አውግዘዋል፡፡

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ሰልፈኞችም ከመንግሥት ጎን በመቆም አንድነታቸውን አጠናክረው ሠላምን ለማስፈን እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።

የሃይማኖት አባት ቄስ ፀዳሉ ጌታቸው በሰጡት አስተያየት የኦነግ ሸኔ ድርጊትን በመቃወም አደባባይ መውጣታቸውን ተናግረዋል።

 ሠላም እንዲመጣ እንደሚጸልዩና ሕዝቡንም ስለ ሰላም እንደሚያስተምሩ አመልክተዋል።

አቶ መልካሙ ታደሰ በበኩላቸው በከተማው ችግር አለመከሰቱን በመጥቀስ ተጠብቆ የቆየውን ሰላም ለማስቀጠል ከፀጥታ ኃይሉ ጋር በመቀናጀት የኦነግ ሸኔን ድርጊት ለማክሸፍ እንደሚሰሩ አመልክተዋል፡፡

“የህወሀት ተላላኪ በሆነው ኦነግ ሸኔ የሚፈጸሙ ግድያዎችና ዘረፋዎችን ለመቃወም ሰልፍ ወጥቻለሁ” ያሉት ደግሞ በከተማው ቀበሌ 02  ነዋሪ አቶ ሠይድ ዓለሙ ናቸው ።

የቡድኑን እኩይ ድርጊት ለማክሸፍ ከመንግሥት ጎን እንደሚቆሙ አስታውቀዋል፡፡

የከተማው ከንቲባ አቶ ዋሲሁን ጉደታ በበኩላቸው የኦነግ ሸኔ የከተማውን ሕዝብ በማለያየት በመካከሉ መተማመን እንዳይኖር እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ቡደኑ የሕወሐት ተልዕኮን ለማሳካት እየተንቀሳቀሰ በመሆኑ ሕዝቡ የነበረውን አንድነቱን አጠናክሮ የከተማውን ሠላም እንዲጠብቅ አሳስበዋል፡፡

በተመሳሳይ በዞኑ በሚገኙ ሲቡ ስሬ፣ ጉደያ ቢላ፣ ጎቡ ሰዮ፣ ዋማ አገሎ፣ ቢሎ ቦሼ፣ ዋዩ ቱቃ፣ ጉቶ ጊዳ፣ ኑኑ ቁምባ፣ ጅማ አርጆ፣ ሌቃ ዱለቻ፣ ዲጋና፣ ኪረሙ ወረዳዎች ነዋሪዎች ኦነግ ሸኔን በመቃወም የአደባባይ ሰልፍ ውጣታቸውን የዞኑ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዘላለም ሦሪ አስታወቀዋል፡፡