በተፋሰስ ልማት ያገኘነው ውጤት ተነሳሽነት ፈጥሮልናል - አርሶ አደሮች

60

መቱ፣  ጥር 7/2013(ኢዜአ)  ላለፉት ዓመታት ባከናወኗቸው የተፋሰስ ልማት ስራዎች ያገኙት ውጤት ለበለጠ ስራ ተነሳሽነት የፈጠረላቸው መሆኑን በቡኖ በደሌ ዞን የበደሌ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ።

በዞኑ የዘንድሮው የበጋ ወቅት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ከ112 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን በማሳተፍ ተጀምሯል።


በበደሌ ወረዳ ሀሮ ቀበሌ በልማቱ ላይ የተሳተፉ አርሶ አደሮች በሰጡት አስተያየት ቀደም ባሉት አመታት ባከናወኑት የተፋሰስ ልማት ስራ የአፈር ለምነት በመጨመርና እርጥበት በአካባቢ በመፍጠር ያሰገኘላቸው ውጤት ለበለጠ ስራ አነሳስቷቸዋል።

አርሶ አደር ተርፋ ጌሲሳ እንዳሉት በበጋው ወቅት በሰሩት የጎርፍ መቀልበሻ ቦይ ዳርቻ የእንስሳት መኖ በመትከል ተጠቃሚ እየሆኑ ነው።

"ከዚህ ቀደም ግጦሽ ፍለጋ እንስሳትን ራቅ ወዳለ ቦታ በማሰማራት የማባክነውን ጊዜና ጉልበት ቆጥቦልኛል" ብለዋል።


የእንስሳት መኖ በበቂ መጠን በማግኘታቸው ልማቱን በማስፋፋት ከብት ለማድለብ አቅደው እየሰሩ እንደሆነም ተናግረዋል።

ለምነቱ ተሟጦ በነበረ ሁለት ጥማድ ተዳፋት መሬት ላይ የሰሩት እርከንና የጎርፍ መቀልበሻ የአፈር ለምነት በመጨመር  ምርታማነትን እንዳሳደገላቸው  የገለጹት ደግሞ ሌላኛው የቀበሌው ነዋሪ አርሶ አደር አለማየሁ ፍሪሳ ናቸው።

ከሀያ አመታት በላይ ደርቆ ለእንስሳት መዋያ ሲያገለግል የነበረ ሶስት ጥማድ የመስኖ ማሳ እርጥበት በመያዙ ካለፉት ሶስት አመታት ወዲህ የጓሮ አትክልትና በቆሎ ማልማት እንደጀመሩ ገልጸዋል።

"በአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራው ውጤቱን ማየቴ ተነሳሽነት ፈጥሮልኛልም" ብለዋል።

በቡኖ በደሌ ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ፅህፈት ቤት የአዝርዕት ልማት ባለሙያ አቶ ሽብሩ ቶላ የዘንድሮው የበጋው አፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በዘጠኝ ወረዳዎች ውስጥ በሚገኙ 230 የገጠር ቀበሌዎች ከ112ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን በማሳተፍ ከትናንት በስቲያ ተጀምሯል።

በስራው 230 ተፋሰሶችን ተከትሎ የሚገኝ ከ65 ሺህ 777 ሄክታር በላይ መሬት እንደሚለማ ተናግረዋል።

አርሶ አደሮቹ በሳምንት በአማካይ አራት ቀናት እንደሚሳተፉና ስራው ለ45 ቀናት እንደሚቆይ አስታውቀዋል።


በዞኑ በተለያዩ ምክንያቶች የተጎዳ 7 ሺህ 237 ሄክታር መሬት ከሰውና እንስሳት ንክኪ እንደሚከለልም ገልፀዋል።


የዘንድሮው የበጋው ወራት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራው በክልል ደረጃ ቅዳሜ ጥር 1 ቀን 2013 ዓ.ም የክልል ፕሬዝዳንት በተገኙበት በምዕራብ ሀረርጌ ዞን በይፋ መጀመሩ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም