ታሪካዊ ቦታዎችን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ እየተሰራ ነው ... ዶክተር ሂሩት ካሳው

94

ደሴ፤ ጥር 7/2013(ኢዜአ)መንግስት ታሪካዊ ቦታዎችን በማልማት የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው ገለጹ።

በደቡብ ወሎ ዞን የተለያዩ መሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ምረቃ ትናንት ተካሄዷል።

ሚኒስትሯ በምረቃ ሥነ- ሥርዓቱ እንዳሉት ኢትዮጵያ ለሌሎች ሃገራት የሚተርፍ በርካታ ባህል፣ ወግና ታሪክ ያላት ሀገር ናት።

ወጣቱ ትውልድ ለዘመናት ዘልቆ ከዚህ የደረሰውን ትክክለኛውን የአባቶቻን ታሪክ ተረድቶ የኢትዮጵያን የአንድነትና አብሮነት እሴቶችን በማጎልበት ማስቀጠል እንዳለበት ተናግረው፤ ለዚህ እንዲያግዝም መንግስት ታሪካዊ ቦታዎችን በማልማት የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

የውጫሌ ውል የተፈረመበት የይስማ ንጉስ ቤተ ሙዚየም የዚሁ ተጨባጭ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያን አንድነትና አብሮነት በሚያሳይ አግባብ መገንባቱን ተናግረዋል።

ሙዚየሙ አስፈላጊው ሁሉ ግብዓት ተማልቶለት ለጉብኝት ክፍት እንዲሆን መንግስት የድርሻውን እንደሚወጣም ዶክተር ሂሩት አስታውቀዋል።

ሙዚየሙ ታሪካዊ ይዘቱን ጠብቆ በተያዘለት ጊዜና ጥራት እንዲጠናቀቅ  ድጋፍና እገዛ ላደረጉ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አገኘሁ ተሻገር በበኩላቸው መሰረተ ልማቶች አስፈላጊውን ሁሉ አገልግሎት እንዲሰጡ ህብረተሰቡ በባለቤትነት እንዲጠብቀው  አሳስበዋል።

ታሪካዊ ሙዚየሙንና ሌሎች ተመርቀው ለአገልግሎት የተዘጋጁ መሰረተ ልማቶችም መንግስት ከፍተኛ መዋለ ንዋይ ያፈሰሰባቸው መሆናቸውን ጠቅሰው፤ የተጓደሉ ግብዓቶችም እንዲሟል ይደረጋል ብለዋል።

ሙዚየሙ የጥቁር ህዝቦች ድልና የአፍሪካ ኩራት በመሆኑ ታሪኩ በሌሎች ዘንድ እውቅና እንዲኖረውና የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆን ተቀናጅቶ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

የክልሉ ህዝብ የልማት  ተጠቃሚ እንዲሆን በጥብቅ ክትትልና ድጋፍ እየተሰራ እንደሚገኝም አቶ አገኘሁ ተናግረዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሰይድ መሃመድ  እንዳሉት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነቡ መሰረተ ልማቶች የህዝቡን የቀደመ የልማት ጥያቄ ለመፍታት ያግዛሉ።

በልማት ስራዎቹ ወቅት የተለያዩ ፈተናዎች ቢገጥሙንም ህዝቡን የመፍትሄው አካል አድርጎ ከጎን በማሳለፍ በተከናወነው ስራ ለዚህ የድል ቀን ልንደርስ ችለናል ብለዋል።

ለአድዋ ድል መነሻ የሆነው ታረካዊ ስፍራ በማልማትም ትውልዱ ከታሪኩ ድል አድራጊነትን በመማር የራሱን ዘመን ታሪክ እንዲሰራ ያነሳሳል ሲሉም ገልጸዋል።

 ታሪካዊ ቦታውን ከመገንባት ባለፈም የእርስ በእርስ መማማሪያ እንዲሆን ይደረጋል ያሉት አቶ ሰይድ፤ በተለይም የወሎ የአንድነትና መቻቻል ተምሳሌት እንዲሰፋ እድል የሚፈጥር መሆኑን አስረድተዋል።

በልማት ፕሮጀክቶቹ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ከፌደራል፣ ከክልል ፣ ከዞንና ከወረዳ የመጡ አመራሮች፣ የሃገር ሽማግለዎችን ጨምሮ ሌሎችም የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

ዛሬ ደግሞ  የኮምቦልቻ ጠቅላላ ሆስፒታልና ሌሎች የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች እንደሚመረቁ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም