በጎንደር ከተማ ለጥምቀት በአል ጊዜያዊ ችሎት ተቋቋመ

119

ጎንደር፣ ጥር 7/2013 (ኢዜአ) በጎንደር ከተማ በጥምቀት በአል ላይ ለሚፈጸሙ ወንጀሎች አፋጣኝ የህግ ውሳኔ ለመስጠት የሚያግዝ ጊዜያዊ ችሎት መቋቋሙን ፖሊስ አስታወቀ፡፡

የከተማው ፖሊስ መምሪያው ሃላፊ ኮማንደር አየልኝ ተክሎ ለኢዜአ እንደገለጹት ጊዚያዊ ችሎቱ ፖሊስን ጨምሮ ዳኞችና አቃብያነ ህጎችን ያሟላ ነው፡፡

ጊዜያዊ ችሎቱ የጥምቀት ስርአቱ በሚከናወንበት የበአሉ አካባቢ በሚፈጸሙ የቡድንና የግለሰቦች ስርቆትና ማጭበርበር ወንጀሎችን አጣርቶ አፋጣኝ የፍርድ ውሳኔ የሚሰጥ መሆኑን ገልፀዋል።

በተጨማሪም ሌሎች የበአሉን ስርአት የሚያውኩ ህገ ወጥ ተግባራትን በሚፈጽሙ ግለሰቦች ላይም ችሎቱ ምስክሮችን በማሰማት አስፈላጊውን የህግ አገልግሎት እንደሚሰጥም ተናግረዋል፡፡

ፖሊስ በአሉ ያለ ፀጥታ ስጋት በሰላም እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ዝግጅት አጠናቋል ያሉት ኮማንደሩ "በከተማው የሚገኙ ሰባት ፖሊስ ጣቢያዎችም በተጨማሪ ፖሊስ ሃይል እንዲጠናከሩ" ተደርጓል ብለዋል።

በበአሉ ለመታደም ወደ ከተማው የሚገቡ የውጭ ሀገር ዜጎች በሚያርፉባቸው አካባቢዎች በቂ የጥበቃ ሃይል ተመድቦ ወደ ስራ መግባቱን ተናግረዋል፡፡

የታቦት ማደሪያዎችና ጥምቀተ ባህሩ የሚገኝበት የአጼ ፋሲለደስ መዋኛ ስፍራም በቂ የፖሊስ ሃይል ተመድቦ የጥበቃ ስራ ከወዲሁ  መጀመሩን አመልክተዋል።

የከተማው ሰላምና የህዝብ ደህንነት መምሪያ ሃላፊ አቶ ናትናኤል ጎሹ በበኩላቸው "ጥበቃ የሚያስፈልጋቸው የከተማው ዋና ዋና መግቢያ በሮችና ኬላዎች የፀጥታ ቁጥጥር ስራ እየተከናወነ ነው" ብለዋል፡፡

በአሉ እስከሚያበቃ ድረስ ማናቸውም የጦር መሳሪያ የታጠቀ ግለሰብ ትጥቅ ይዞ ወደ ከተማው መግባትም ሆነ መዘዋወር  እንደማይችል መመሪያ መተላለፉን ተናግረዋል፡፡

ለበአሉ ማድመቂያ በሚል የጦር መሳሪያም ሆነ ርችት መተኮስ በጥብቅ የተከለከለ መሆኑንም ሃላፊው ተናግረዋል፡፡

"በበአሉ ቦታ አልኮል ጠጥቶ በስካር መንፈስ ፀጥታ ለማወክ ሙከራ በሚያደርጉ ግለሰቦች ላይ የፀጥታ መዋቅሩ ጥብቅ ቁጥጥር ይደረጋል" ብለዋል።

በጎንደር ከተማ በታላቅ ሃይማኖታዊ ስርአት በሚከበረው የጥምቀት በአል በርካታ የውጪ ሀገራት ቱሪስቶች፣ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ ታላላቅ እንግዶችና የእምነቱ ተከታይ የከተማው ነዋሪዎች ይታደማሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም