በህንድ ሊሰጥ የታቀደው የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ክትባት የድሆችን አቅም ይፈትናል ተባለ

59

ጥር 7/2013 (ኢዜአ) ህንድ ከያዝነው ጥር ወር ጀምሮ ለዜጎቿ የኮሮና መከላከያ ክትባት ለመስጠት ብታቅድም የክትባቱ ዋጋ የድሆችን አቅም ሊፈትን እንደሚችል ተገለጸ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ናረንድራ ሞዲ ከፍተኛ ባለስልጣኖቻቸውን በበይነ መረብ ባነጋገሩበት ወቅት በመጀመሪያው ምዕራፍ 30 ሚሊየን ክትባቶችን በማስገባት በቅድሚያ ለቫይረሱ ስርጭት ተጋላጭ ለሆኑ የጤና ባለሙያዎችን ጨምሮ ሌሎች የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል ከፊት ሆነው እየሰሩ ላሉ ሰራተኞች እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

በተጨማሪም የሀገሪቱ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሀርሽ ቫርድሃን ሀገራቸው ለ1 ነጥብ 3 ቢሊዬን ዜጎቿ ክትባቱን ለማዳረስ እየሰራች መሆኗን ማረጋገጫ መስጠታቸውን በዘገባው ተገልጿል።

የሀገሪቱ ባለስልጣናት ይህን ይበሉ እንጂ በቀጣይ በሀገሪቱ ክትባቱን ለማቅረብ የታቀደው በሽያጭ ሲሆን ለዚህም የአንዱ ክትባት ዋጋ 13 የአሜሪካን ዶላር ዋጋ ተተምኖለታል፡፡

ይህም ከሀገሪቱ ህዝብ መካከል 70 በመቶ የሚሆነው ህዝብ ከድህነት ወለል በታች የሚገኝና የቀን ገቢውም ከ2 የአሜሪካ ዶላር በታች ለሆነው የህብረተሰብ ክፍል ክትባቱን ለማግኘት ይከብዳል ነው የተባለው።

ህንድ ለመስጠት ያሰበቻቸውን ክትባቶች በጠበቀ ቁጥጥር ጥቅም ላይ እንዲውሉ ለሁለት የግል የመድሃኒት አምራች ድርጅቶች በዚሁ ወር ፈቃድ መስጠቷን የካቶሊክ ኤዢያን ህብረት የዜና ምንጭ ዘግቧል።

ጥቅም ላይ ከሚውሉት ክትባቶች መካከል ኮቪሺልድ የተባለው በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የህንድ ሴሩም ኢንስቲትዩት የተመረተ ሲሆን፤ ሁለተኛው ኮቫክሲን መድሃኒት ደግሞ በሀገሪቱ በሚገኘው ባህራት ባዮቴክ በተባለ የምርምር ማዕከል የተዘጋጀ መሆኑን የሀገሪቱ የመድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን መግለጻቸውን የዜና ምንጩ አስነብቧል፡፡

በህንድ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ10 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ሲሆን ህይወታቸውን ያጡ ደግሞ ከ150 ሺህ በላይ መሆኑን መረጃው አስታውሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም