ኢዜማ የጋራ የቃል- ኪዳን ሰነዱን በማክበር ለምርጫው ለመወዳደር በዝግጅት ላይ መሆኑን አስታወቀ

1045

ጥር 6/2013 ኢዜማ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ የፈረሙትን የቃል- ኪዳን ሰነድ በማክበር ለምርጫው ለመወዳደር በዝግጅት ላይ መሆኑን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ /ኢዜማ/ ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

በመግለጫውም የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ የፈረሙትን የቃል- ኪዳን ሰነድ በማክበር ለምርጫው ለመወዳደር በዝግጅት ላይ መሆኑን አስታውቋል።

ኢዜማ በምርጫው ለመሳተፍ የተለያዩ ዝግጅቶችን በማድረግ ላይ መሆኑን በመግለጽ ከፓርቲዎች ጋር የተገባውን የጋራ ቃል-ኪዳን ሰነድ በመፈረም ለአባላቱ ሥልጠና መስጠቱን ገልጿል፡፡

በአገሪቷ የሚገኙ ሁሉም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለምርጫ ዝግጅት በሚያደርጉበት ወቅት የተፈረመውን የቃል- ኪዳን ሰነድ ማክብር መሆን እንዳለበትም በመግለጫው ጠቅሷል።

ዘንደሮ የሚካሄደው ምርጫ አገሪቷ ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ ወደ ተሻለና የተረጋጋ መንገድ የሚመልስና ትክክለኛ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እንዲጠናከር የሚያደርግ መሆኑንም ገልጿል።

ምርጫው ዴሞክራሲያዊ እና ተቀባይነት ያለው እንዲሆን የኅብረተሰቡ ተሳትፎ ከፍተኛ መሆን አለበት ያለው ኢዜማ ህዝቡም በነቂስ በሂደቱ ሁሉ እንዲሳተፍ ጥሪውን አቅርቧል፡፡

የዘንደሮውን ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ ስኬታማ ለማድረግ የአገሪቱን ሰላምና ደህንነት ማስከበር ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባም ገልጿል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድም ምርጫው ተዓማኒ እና ህግ የሚከበርበት ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩሉን ኃላፊነት መወጣት አለበት ብሏል በመግለጫው፡፡

ቀጣዩን አገራዊ ምርጫ የተሳካና ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በነጻነት የምርጫ እንቅስቃሴያቸውን እንዲያደርጉ ሰላም እና ደህንነት ማስጠበቅ ላይ መንግስት ይበልጥ ትኩረት ማድረግ እንዳለበት አመልክቷል፡፡

አሁን በአገሪቷ አንዳንድ አካባቢዎች ያሉ የሰላም መደፍረሶች እውነተኛና ዘላቂ የሆነ የህዝብ አስተዳደር ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት እንዳያደናቅፉ ሲልም ኢዜማ ስጋቱን ገልጿል።