የጃፓን መንግስት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ በቀለ ሆርዶፋ የጃፓን የክብር ኒሻን ሽለመ

82

አዲስ አበባ፤ ጥር 6/2013(ኢዜአ) የጃፓን መንግስት ለኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ በቀለ ሆርዶፋ የጃፓን የክብር ኒሻን ሽልማት ሰጠ።

በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሚስ ኢቶ ታካኮ መኖሪያ ቤት በተካሄደ ስነ ስርዓት አቶ በቀለ ሽልማቱን ከአምባሳደሯ ተቀብለዋል።

የተበረከተላቸው ሽልማት በወርቅና ብር የተሰራ ባለ ኮከብ ቅርጽ ያለው ሜዳሊያ መሆኑም ታውቋል።

አቶ በቀለ ሆርዶፋ ሽልማቱ የተሰጣቸው የኢትዮጵያ ጃፓንን የኢኮኖሚ ግንኙነት ለማጠናከር ባደረጉት አስተዋጽኦ እንደሆነ ተገልጿል።

አቶ በቀለ የኢትዮጵያና ጃፓን የወዳጅነት ቡድን ምክትል ሊቀመንበር ሆነው ያገለገሉ ሲሆን የጃፓን የአሰራር ፍልስፍና ካይዘን በኢትዮጵያ የተለያዩ ተቋማት ተግባራዊ እንዲሆን ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጋቸው ተመልክቷል።

በተጨማሪም የኢትዮጵያና ጃፓን ፓርላማዎች ግንኙነት እንዲጠናከር አስተዋጽኦ እንዳበረከቱም ተጠቅሷል።

አቶ በቀለ ሆርዶፋ እ.አ.አ በ2019 ኢትዮጵያና ጃፓን ያላቸውን ግንኙነት እንዲጎለብት ላከናወኑት ተግባር ከጃፓን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የምስጋና ሽልማት እንደተበረከተላቸው የሚታወስ ነው።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ እና አቶ ነዋይ ገብረአብ የጃፓን የክብር ኒሻን ተሸላሚዎች ነበሩ።

የጃፓን መንግስት የክብር ኒሻን መስጠት የጀመረችው እ.አ.አ ከ1875 ጀምሮ ሲሆን፤ ሽልማቱ የሚበረከተው የሁለትዮሽ ግንኙነት በማጠናከር አስተዋጽኦ ላደረጉ የውጭ አገር ዜጎች ነው።

በስነ ስርዓቱ ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ ዲፕሎማቶችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም