በአፋር ክልል 36 የህግ ታራሚዎች በይቅርታ ተለቀቁ

51

ሠመራ ጥር 06/2013 (ኢዜአ) በአፋር ክልል የይቅርታ መስፈርትን አሟልተው የተገኙ 36 የህግ ታራሚዎች በይቅርታ ከእስር እንዲለቀቁ መደረጉን የክልሉ ዋና ጠቅላይ አቃቢ ህግ ወይዘሮ ፋጡማ መሐመድ አስታወቀ።

ወይዘሮ ፋጡማ  እንደገለጹት  ጉዳያቸው ለክልሉ የይቅርታ ቦርድ ቀርቦ  ከእስር እንዲለቀቁ የተወሰነላቸው  በተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች ተፈርዶባቸው ይቅርታ እንዲደረግላቸው ከጠየቁ  102  የህግ ታራሚዎች መካከል ነው።

የህግ ታራሚ ይቅርታ እንዲደረግለት በሠራው ወንጀል ከመፀፀቱ ባለፈ ቢያንስ አንድ ሶስተኛ የሚሆነውን የእስር ጊዜውን ማጠናቀቅ ይጠበቅበታል ብለዋል ።

በዚህም መስፈርቱን አሟልተው የተገኙ 36  ታራሚዎች ከትናንት ጀምሮ  በይቅርታ ተለቀው ወደ   ህብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ  የክልሉ  የይቅርታ ቦርድ ተገቢነቱን መርምሮ መወሰኑን አስታውቀዋል።

የክሉሉ ማረሚያ ቤቶች ጽህፈት ቤት ምክትል ሃላፊ አቶ መሐመድ አህመድ በበኩላቸው በክልሉ የሚገኙ ታራሚዎች   አምራች ዜጋ እንዲሆኑ የቀለምና ሙየዊ ሥልጠናዎች እየተሰጣቸው መሆኑን ገልጸዋል።

በይቅርታ የተለቀቁት ታራሚዎች በማረሚያ ቤት ቆይታቸው ያገኙትን የህግ ግንዛቤ እና የሙያ ትምህርት ተጠቅመው ከራሳቸው አልፎ   የበደሉትህ ህብረተሰቡ በመካስ አምራች ዜጋ መሆን  እንደሚጠበቅባቸው አስታውቀዋል።

ይቅርታ ከተደረገላቸው የህግ ተራሚዎች መካካል አቶ አሊ ከቢር በሰጡት አስተያየት በቆይታቸው   የወንጀልን አስከፊነት በመገንዘብ መታረማቸውን ገልጸው  በቀሪ ህይወታቸው አምራች ሆነው  ከህብረተሰቡ ጋር በሠላም   ለመኖር መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

በክልሉ ትናንት ለታራሚዎች ይቅርታ የተደረገው  በዓመቱ  ሁለት ጊዜ  ይቅርታ ለመስጠት  የተያዘው እቅድ አካል መሆኑን ከክልሉ ጠቅላይ አቃቢ ህግ   ገለጸ ለመረዳት ተችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም