የክልሉን ሠላም ለማረጋገጥ መንግስት አበክሮ ይሰራል -የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር

60

ሀዋሳ ጥር 6/2013 (ኢዜአ) የክልሉን ሠላምና ደህንነት ለማረጋገጥ የፖሊስ ኃይሉን በስልጠና፣ ሎጂስቲክስና ሁሉም ቦታ ተደራሽ ለማድረግ መንግስት አበክሮ እንደሚሰራ የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው አስታወቁ።

የክልሉ ፖሊስ ኮሌጅ  ያሠለጠናቸው 604 የልዩ ኃይል ፖሊሶችን ዛሬ በይርጋለም -አፖስቶ አስመርቋል።

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ የተገኙት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ  ከውስጥም ይሁን  ከውሰጥ  ሀገሪቱን የሚጎዳና የሚዳፈር ኃይል ቦታ እንደሌለው አስታውቀዋል።

በተለይ ኢትዮጵያ በውስጥ ጉዳያ ተጠምዳለች ብለው ሉአላዊነቷን ለመዳፈር የሚቋምጡ ኃይሎች እየተስተዋሉ መሆኑን ጠቅሰው እነዚህን ለማንበርከክ በሚደረገው እንቅስቃሴ የክልሉ መንግስት የድርሻውን ለመወጣት  በሙሉ ቁመና ላይ እንደሚገኝ አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያዊያን ለማንነታችንና ለክብራችን ሟች መሆናችንና ጠላቶቻችንንም በጀግንነት ድል እንደምናደርግ ልናረጋግጥላቸው እንወዳለን  ብለዋል።

በትግራይ ክልል ህግን ለማስከበር በተካሄደው ዘመቻ የሀገር መከላከያ  ሠራዊት፣ ሌሎችም  የፀጥታ አካላትና መላው ህዝብ ያሳዩት አንድነትና ትብብር የሚያኮረ መሆኑን አቶ ርስቱ ጠቅሰዋል።

ይህም ሀገሪቱ ከጠላት መከላከል የሚያስችል  ቁመና ላይ እንደምትገኝ  ለዓለም  ማህበረሰብ  ያስመሰከረ ጀግንንት መሆኑን አውስተዋል።

የክልሉን ሠላምና ደህንነት ለማረጋገጥም የፖሊስ ኃይሉን በስልጠና፣ በሎጂስቲክስና በሁሉም ቦታ ተደራሽ ለማድረግ የክልሉ መንግስት አበክሮ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር ነብዩ ኢሳያስ በበኩላቸው ፖሊስነት አገልግሎት ሰጪነት ብቻ ሣይሆን በማንኛውም ሁኔታ ለህዝብ ደህንነት እራስን አሰልፎ መስጠትን እንደሚጠይቅ ገልጸዋል።

በተለይ ወንጀልን አምርሮ የሚጠላ ጥበብና ሳይንስ መሆኑን አመልክተው በዚህ ረገድ ኮሚሽኑ በህግ የተሰጠውን ተልዕኮ ለመወጣት የአባላቱን አቅም  በስልጠና በመገንባት  እየተጋ   እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

የአሁኑ ሠልጣኞችም ወደ ሥራ ሲሰማሩ ፖሊሳዊ አገልግሎትንና ተደራሽነትን በማሳደግ የክልሉን ሠላም በዘላቀነት ለማስከበር ያስችላል ብለዋል።

 ኮሌጁ በፖሊሳዊ ሳይንስ አሠልጥኖ ዛሬ  ያስመረቃቸው 604 የልዩ ኃይል ምልምል መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ  የክልሉ ፖሊስ ኮሌጅ ዋና ዳይሬክተር ኮማንደር  አብርሀም  ቲርካሶ ናቸው።

ሠልጣኞቹ በቆይታቸው የወንጀል መከላከል ጽንሰ ሃሳብ፣ ግጭት መቆጣጠርና አፈታት፣ የተግባቦትና በሌሎችም መስኮች እውቀት እንዲጨምቱ ተደርጓል ብለዋል።

በበንድፈ ሀሳብና በተግባር ያገኙትን ክህሎት በመጠቀም የህብረተሰቡን ደህንነት ለማረጋገጥ  እንዲተጉ መልክዕታቸውን አስተላልፈዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ተመራቂዎች ለፖሊሲያዊ ሥነ ምግባር  በመገዛት  ህዝባቸውን በማንኛውም ቦታ ተመድበው ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም