የአፋር ክልል ምክር ቤት ጉባኤ ሹመቶችን በማጽደቅ ተጠናቀቀ

53

ሠመራ፤ጥር 6/2013 (ኢዜአ) የአፋር ክልል ስድስተኛ ዓመት የስራ ዘመን ሁለተኛ አስቸኳይ ጉባኤ ሹመቶችን በማጽደቅና የሥራ አቅጣጫን በማስቀመጥ ተጠናቀቀ።

ምክር ቤቱ ከጥር 5/2013 ዓ.ም ጀምሮ ሲያካሄድ የቆየውን ጉባኤ ዛሬ ሲያጠናቀቅ ሹመቶችን ያጸደቀው የክልሉ ርዕሰ መሰተዳደር አቶ አወል አርባ ያቀረቧቸውን የጠቅላይ ፍርድ ቤትና የዋናው ኦዲት መስሪያ ቤት ሃላፊዎችን ነው።

በዚህ መሰረትም፣

1ኛ. አቶ ሙሳ አብደላ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት

2ኛ. አቶ አብዱሠላም አህመድ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት እና

3ኛ. አቶ አህመድ መሀመድ የክልሉ ዋና ኦዲት መስሪያ ቤት ሀላፊ ሆነው ተሹመዋል።የምክር ቤቱ ጉባኤ የቀረቡለትን የእነዚህን ሃላፊዎች ሹመት በመቀበል በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።

በተጨማሪም ምክር ቤቱ የስድስተኛው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ በአፋር ክልል ያለምንም የጸጥታ ችግር ሠላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በየደረጃዉ የሚገኙ የምክር ቤቶች አባላት ህብረተሰቡን በማንቃት የማስተባባርሚናቸውን በአግባቡ እንዲወጡም አሳስቧል።

ለህዝቦች አብሮነት ጠንቅ ሊሆኑ የሚችሉ ችግሮችን ከወዲሁ ትኩረት ተሰጥቷቸዉ እንዲፈቱ ምክር ቤቱ አቅጣጫ አስቀምጧል።

የኮሮና ወረርሺኝን ለመከላከል በመንግስትና ሃይማኖት ተቋማት እንዲሁም ትምህርት ቤቶችና ሌሎች ሰው በሚበዛባቸው የአገልግሎት መስጫ ድርጅቶች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል የመጠቀም ልምድ እንዲጎለብት የምክር ቤቱ አባላት የመሪነት ሚናቸው እንዲወጡ በክልሉ ጤና ቢሮ የቀረበውን ምክረ-ሃሳብ ላይ የጋራ መግባባት ላይ በመድረስ ጉባኤው ተጠናቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም