ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ከኦስትሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ተወያዩ

1910

ጥር 6/2013 (ኢዜአ) ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ከኦስትሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሌክሳንደር ሻለንበርግ ጋር ተወያዩ።

በነበራቸው ውይይት ሁለቱ አገሮች ለረዥም ጊዜ የቆየውን ወዳጅነት ይበልጥ ለማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መክረዋል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቋሚ ተጠሪ አምባሳደር ወይንሸት ታደሰ ከውይይቱ በኋላ በሰጡት ማብራሪያ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴና የኦስትሪያ  ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሌክሳንደር ሻለንበርግ በሁለቱ አገራት ተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ መምከራቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያና ኦስትሪያ በተለይ በንግድ፣ ኢንቨስትመንትና ሌሎች ዘርፎችም ትብብራቸውን ማጠናከር ስለሚችሉባቸው ጉዳዮች አንስተዋል።

በግብርና፣ ኢነርጅና ሌሎችም መስኮችም ይበልጥ የተጠናከረ ስራ ለማከናወን በሚችሉባቸው ሁኔታዎችም ላይ መወያየታቸውን አምባሳደር ወይንሸት ገልጸዋል።

በትግራይ ክልል የተወሰደውን የህግ ማስከበር እርምጃና በአሁኑ ወቅት እየተደረገ ያለውን መልሶ የመገንባት ተግባርም ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ገለፃ አድርገውላቸዋል።

የኦስትሪያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሌክሳንደር ሻለንበርግ በበኩላቸው ኦስትሪያ በንግድ፣ ኢንቨስትመንትና በልማት ትብብር ቅድሚያ ከምትሰጣቸው አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ መሆናን ገልጸዋል።

በትግራይ ክልል የተጀመረው መልሶ የመገንባትና ሰላም የማስፈን ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸው አገራቸው ፕሮጀክት በመቅረጽ ለማገዝ ዝግጁ እንደሆነች አረጋግጠዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ በሚኖራቸው የሁለት ቀናት ቆይታ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን እንደሚጎበኙ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያና ኦስትሪያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተጀመረው እኤእ በ1905 መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።