የጥምቀት በዓልን ምክንያት በማድረግ በመጪው እሁድ በአዲስ አበባ ከተማ የጽዳት ዘመቻ ይካሄዳል

1571

ጥር 6/2013 (ኢዜአ) የጥምቀት በዓልን ምክንያት በማድረግ በመጪው እሁድ በአዲስ አበባ ከተማ የጽዳት ዘመቻ እንደሚካሄድ የአዲስ አበባ ከተማ የደረቅ ቆሻሻ አስተዳደር ኤጀንሲ አስታወቀ።

ኤጀንሲው የጽዳት ዘመቻውን በሚመለከት ከባለድርሻ አካላትና ከበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡

የኤጀንሲው ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር እሸቱ ለማ የጽዳት ዘመቻው በዓሉ በሚከበርባቸው የእምነት ቦታዎችና አካባቢዎች እንደሚከናወን ተናግረዋል።

በዘመቻው ለሚሳተፉ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች የቆሻሻ አወጋገድን በሚመለከት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ መከናወኑንም ነው የገለጹት።

የከተማዋ ነዋሪዎች በዓሉን ምክንያት በማድረግ የሚኖሩበትን አከባቢ እንዲያጸዱም ጥሪ አቅርበዋል።

በቅርቡ የከተማ አስተዳደሩ በደረቅ ቆሻሻ አሰባሰብና በአካባቢ ጥበቃ ያስመረቃቸው ወጣቶች በመዲናዋ የጽዳት ስራ በዘላቂነት ለማስቀጠል በሚከናወኑ ተግባራት ላይ እንደሚሳተፉም ተናግረዋል።

በተጨማሪ ኤጀንሲው ከበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ፣ከመንደር ብሎክ አደረጃጀቶችና ከስፖርት ቤተሰቡ ጋር በቅንጀት እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች በጽዳት ስራዎች ላይ በቀጣይነት እንዲሳተፉ ጥሪ ያቀረቡት ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ  የወጣቶች የበጎ ፍቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ ሃላፊ አቶ አብረሃም ታደሰ ናቸው።

በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ለአትክልትና ፍራፍሬ መሻጫ ሲያገለግል የነበረውን የጃንሜዳ አካባቢን በማጽዳት ረገድ ላበረከቱት አስተዋጽኦም ሃላፊው ምስጋና አቅርበዋል።