በጅማ ዩኒቨርሲቲ ስታድየም ነገ ለሚጀመረው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ዝግጅት ተደርጓል- ካምፓኒው

2019

ጅማ ጥር 06/2013 (ኢዜአ) በጅማ ዩኒቨርሲቲ ኢንተርናሽናል ስታዲየም ነገ ለሚጀመረው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ዝግጅት መደረጉን የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሼር ካምፓኒ አስታወቀ።

የካምፓኒው ስራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፈ ለኢዜአ እንደገለጹት የጅማ ዩኒርቨሲቲ ስፖርት አካዳሚ ኢንተርናሽናል ስታዲየም ነገ ለሚጀመረው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ዝግጅት ተደርጓል።

ዝግጅቱ ከልምምድ ሜዳ፣ ሆቴል፣ የኮቪድ መከላከልና የጸጥታ ሁኔታ ላይ  ያተኮረና ያካለለ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ልግ 13 ክለቦች ከነገ ጀምሮ ለተከታታይ አምስት ሳምንት በጅማ ዩኒቨርስቲ ስፖርት አካዳሚ ኢንተርናሽል ስታዲዬም ውድድራቸውን እንደሚያካዱ አቶ ክፍሌ አመላክተዋል።

ውድድር ከሚደረግበት ስታዲየም በተጨማሪ በሌሎች አራት ስታዲየሞች ተወዳዳሪ ክለቦች ልምምድ እያካሄዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ጨዋታውን የሚያስተናግደው የጅማ ዩኒቨርሲቲ ኢንተርናሽናል ስታዲየም የመጸዳጃ፣ የማረፊያ፣

የመልበሻ፣ የተሽከርካሪ ማቆሚያ፣ የገላ መታጠቢያ የመሳሰሉ አገልግሎት መስጫዎች የተሟሉለት መሆኑን ተናግረዋል።

ስታድየሙ እስከ 60ሺህ ተመልካች ማስተናገድ እንደሚችል  አቶ ክፍሌ አስታውቀዋል።

የጅማ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የሚዲያና ኮመኒኬሽን ዘረፍ ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ገዛሃኝ አውግቻው በበኩላቸው “ጨዋታው በሰላም ተካሂዶ እንዲጠናቀቅ  ከሚመለከታቸው የጸጥታ መዋቅር ጋር በመቀናጀት በቂ ዝግጅት ተደርጓል” ብለዋል ፡፡