በእንግሊዝ የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ክትባት በመድሃኒት መሸጫ ሱቆች መሰጠት ተጀመረ

88


ጥር 6/2013 በእንግሊዝ ዋና ዋና መንገዶች የሚገኙ የመድሃኒት መሸጫ ሱቆች የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ክትባት ቅድሚያ ለሚሰጣቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ዛሬ መሰጠት ሊጀምሩ መሆኑ ተገለጸ::

ይህን አቅርቦት በመጪዎቹ ሁለት ሳምንታት ውስጥ በሁለት መቶ መድኃኒት መሰጫ ሱቆች ለማቅረብ መታቀዱን ቢቢሲ ዘግቧል።

ይህን ለመጀመሪያ ጊዜ የሚሰጠውን የክትባት ስርጭት እንዲያስተባብሩ ስድስት የመድሃኒት ቅመማ ባለሙያዎች ከሃሊፋክስ፣ ማክሌስፊልድ፣ ዊድነስ፣ ጊዩልድፎርድ፣ ኢድግዌር እና ቴልፎርድ ከተሞች እንደተመረጡ በደብዳቤ እንደተገለጸ ተዘግቧል፡፡

የመድሃኒት ሽያጭ ባለሙያዎች ግን ይህ አይነቱ ስርጭት በዋና ዋና መንገዶች ላይ በሚገኙ የመድሃኒት መሸጫ ሱቆች ብቻ ሳይሆን በበርካታ ስፍራዎችም ተደራሽ መሆን አለበት ማለታቸውን ዘገባው ጨምሮ አስነብቧል፡፡

በእንግሊዝ ሆስፒታሎች፣ በቤት፣ ኦፕራሲዮን በሚሰጥባቸው የህክምና ቦታዎችና የክትባት አገልግሎት መስጫ ማዕከላት ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ክትባት  በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የተመረተው አስትራ ዜኒካ እና በፋይዘር ባዮ ቴክ የተመረተ እንደሆነ ተገልጿል።

በእንግሊዝ ከ2 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ ዜጎች የመጀመሪያውን ዙር ክትባት መውሰዳቸው መረጃው አስታውሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም