ለ500 ኢንተርፕራይዞች ግብአቶች ለማቅረብ ዝግጁ ተደረገ –ኢንዱስትሪ ግብአቶች ልማት ድርጅት

1524

አዲስ አበባ ጥር 6/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብአቶች ልማት ድርጅት በተያዘው ዓመት ለ500 መካከለኛና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ግብአት ለማቅረብ መዘጋጀቱን ገለጸ።

ኢትዮጵያ ወደ ኢንዱስትሪ መር ምጣኔ ሃብት እያደረገች ያለውን ሽግግር እንዲደግፉ ተስፋ የተጣለባቸው አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች በሚፈለገው ደረጃ ማደግ እንዳልቻሉ ይገለጻል።

በዘርፉ የግብአት፣ የፋይናንስ፣ የመስሪያ ቦታ፣ የገበያ ትስሰርና ሌሎችም ችግሮች  በስፋት እንደሚስተዋሉ በተደጋጋሚ ይነሳል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብአቶች ልማት ድርጅት በግብአት በኩል የሚስተዋለውን ችግር ለመፍታት እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሮ የሺመቤት ነጋሽ ለኢዜአ እንደተናገሩት በኢንተርፕራይዞቹ የሚስተዋለውን የግብአት ችግር ለመፍታት የዳሰሳ ጥናት ተደርጓል።

በዚህም ቅድሚያ የሚሰጣቸው የጨርቃጨርቅና አልባሳት፣ የቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያና ሌሎች ዘርፎች ፍላጎታቸው ተለይቷል ብለዋል።

በመሆኑም በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ኢንተርፕራይዞች በድርጅቱ ቅርንጫፎች በኩል ይደገፋሉ ብለዋል ዋና ስራ አስፈፃሚዋ።

በተያዘው በጀት ዓመት ለ500 መካከለኛና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ግብአት ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በአገር ውስጥ የሚገኙ ግብአቶች ግዥ ለመፈጸም ውል መፈፀሙን ጠቅሰው በአገር ውስጥ የማይገኙትን ከውጭ ለማስገባት የውጭ ምንዛሪ ለማስፈቀድ በሂደት ላይ መሆኑን አስረድተዋል።

በድርጅቱ ተከማችተው የነበሩ ግብአቶችን ዋጋ በመከለስ ለኢንተርፕራይዞች እንደሚቀርቡም አረጋግጠዋል።

በተለይ የጨርቃጨርቅ፣ ቆዳና ሌሎችም ዘርፎች የምርት ግብአት በማጣት ስራ ያቆሙ እንዳሉ አስታውሰዋል።

በቀጣይ ግን አንዱ ኢንተርፕራይይዝ ያመረተው ለሌላው ግብአት የሚሆንበትን አሰራር በመፍጠር  ከውጭ የሚገቡትን ደግሞ በአገር ውስጥ ለመተካት እየተሰራ መሆኑን ወይዘሮ የሺመቤት ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ  በማምረቻ (ማኑፋክቸሪግ) ዘርፍ የተሰማሩ 15 ሺህ አነስተኛና ከ4 ሺህ በላይ መካከለኛ አምራቾች አንደሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ።