የተፈጥሮ ሀብት ስራ ተጨባጭ ውጤት እየታየበት ነው - ዶክተር ግርማ አመንቴ

101

አዳማ ጥር 06/2013 (ኢዜአ) ባለፉት አመታት በተከናወኑ የተፈጥሮ ሀብት ስራዎች ተጨባጭ ውጤት እየታየባቸው መሆኑን በምክትል ርዕሰ መስተደድር ማዕረግ የኦሮሚያ የገጠር ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አመንቴ ገለፁ።

የኦሮሚያ ክልልል ከፍተኛ አመራሮችና የስራ ኅላፊዎች በምስራቅ ሸዋ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች የተከናወኑ የተፈጥሮ ሀብት ስራዎችን ዛሬ በመጎብኘት የዘንድሮን የተፋሰስ ልማት ስራም በይፋ አስጀምረዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተደድር ማዕረግ የክልሉ የገጠር ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አመንቴ ለኢዜአ እንደገለፁት በክልሉ ባለፉት ዓመታት  በተከናወኑ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ስራዎች ተጨባጭ ውጤት እየታየ ነው።

በምስራቅ ሸዋ ዞን ሉሜ ወረዳ ጠዴ ቀበሌ ሲንቄ አዮ ማህበር በሚል ተደራጅተው በአካባቢ ጥበቃ ስራ የተሰማሩ አባላት ባከናወኑት ተግባር የተጎዳና የተረቆተ መሬት መልሶ በደን መሸፈኑ በዘርፉ እየመጣ ላለው ተጨባጭ ውጤት ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።

"አካባቢውን ከ20 ዓመት በፊት ሳውቀው መሬቱ ከመጎዳቱ የተነሳ አይደለም በደን መሸፈን ሳር የሚበቅልበት አይመስልም ነበር" ብለዋል።

ባለፉት ዓመታት በተፈጥሮ ሀብት ልማት ላይ በተሰሩ ስራዎች የተራቆቱና የተጎዱ መሬቶች እያገገሙ ከመሆናቸውም ባለፈ በደን ተሸፍነው የገቢ ምንጭ መሆናቸውን ተናግረዋል።

"በሉሜ ወረዳ ጠዴ ቀበሌ ያየነው ውጤት ተጨባጭ ማሳያ ነው" ያሉት ዶክተር ግርማ በክልሉ እየለሙ ካሉት ከ6 ሺህ ተፋሰሶች ውስጥ 1ሺህ 400 የሚሆኑት ለሴቶችና ለወጣቶ  በባለቤትነት መተላለፋቸውን አመልክተዋል ።

በዘርፉ የተሰማሩ ወጣቶችና ሴቶች  ባለፉት ስድስት ወራት ካገኙት ገቢ ከ40 ሚሊየን ብር በላይ መቆጠባቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል ።

በዘንድሮ የተፋሰስ ልማት ትግበራ የዕርከንና ክትር ጨምሮ  የተለያዩ የአፈርና ውሃ ዕቀባ ስራዎች  እየተከናወኑ መሆኑን ዶክተር ግርማ አስታውቀዋል።

የምስራቅ ሸዋ ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ጽሕፈት ቤት ኅላፊ አቶ ከፍያለው ለማ በበኩላቸው በዞኑ በተካሄደው የተፈጥሮ ሀብት ልማት ስራ ውጤት እየተገኘ መሆኑን ተናግረዋል።

በማህበር የተደራጁ 190 ሴቶች በ250 ሄክታር  መሬት ላይ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና እንክብካቤ  ስራ እያከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተፈጥሮ ሀብት ልማትና እንክብካቤ  ስራው የተራቆተው መሬት አገግሞ በደን መሸፈኑን የገለፁት አቶ ከፍያለው በአሁኑ ወቅት ንብ በማነብና በእንስሳት መኖ ልማት ተሰማርተው ውጤታማ መሆናቸውን አመልክተዋል።

"የአካባቢ ጥበቃ ስራ ውጤታማ አድርጎናል" ያሉት ደግሞ በሉሜ ወረዳ ጠዴ ቀበሌ የአዮ ሲንቄ ማህበር አባላል ወይዘሮ ዘውድነሽ መንግሥቱ ናቸው።

አባላቱ ባከናወኑት የተፈጥሮ ሀብት ልማትና እንክብካቤ ስራ ተራቁቶ የነበረው መሬት በማገገሙ በንብ ማነብና የእንሰሳት መኖ ልማት ተሰማርተው ወጤታማ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

እንደ ወይዘሮ ዘውድነሽ ገለጻ  የማህበሩ አባላት አሁን ላይ ከ150 ሺህ ብር በላይ ቆጥበዋል።

ዶከተር ግርማ ባለፉት አመታት የተከናወኑ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ስራዎችን በመጎብኘት የዘንድሮን የተፋሰስ ልማት ስራ አስጀምረዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም