በጦራ ከተማ የእሳት ቃጠሎ ከ1 ሚሊዮን 500 ሺህ ብር በላይ የሚገመት ንብረት አወደመ

1655

ሆሳዕና ጥር 6/2013 (ኢዜአ) በስልጤ ዞን ጦራ ከተማ በደረሰ የእሳት ቃጠሎ ከአንድ ሚሊየን 500 ሺህ ብር በላይ የሚገመት ንብረት መውደሙን ፖሊስ አስታወቀ።

በአደጋው በሰው ህይወት ላይ የደረሰ ጉዳት እንደሌለ ተመልክቷል።

የከተማዋ አስተዳደር ፖሊስ አዛዥ ሳጅን ሬድዋን ደኑር ለኢዜአ እንደገለጹት የእሳት ቃጠሎው የተነሳው  ትናንት ምሽት አንድ ሰዓት አካባቢ በከተማው መልካሜ ቀበሌ በተለምዶ አጠራር ሚቶ መውጫ በተባለው ሥፍራ ከኤሌክትሪክ መስመር ጋር በተገናኘ ነው።

በአደጋው በ21 መኖሪያ ቤቶችና የንግድ ተቋማት ላይ በደረሰ ቃጠሎ ከአንድ ሚሊዮን 500ሺህ ብር በላይ የሚገመት ንብረት ወድሟል ብለዋል።

ህብረተሰቡ ባደረገው  ርብርብ ቃጠሎው የከፋ ጉዳት ሳያደርስ መቆጣጠር እንደተቻለ ጠቁመው በአደጋው በሰው ህይወት ላይ የደረሰ ጉዳት እንደሌለ አመልክተዋል።

የቃጠሎ  መነሻ እየተጣራ ቢሆንም  በአንዳንድ የንግድ ሱቆች ቤንዝን በችርቻሮ የሚሸጡ ስለነበር  ቃጠሎው እንዲባባስ ምክንያት እንደሆነ  የከተማዋ አስተዳደር ፖሊስ  አዛዡ አስታውቀዋል።