የቀደምት ጀግኖች አባቶች መልካም እሴቶቻቸውን ማስቀጠል እንደሚገባ ምሁራን ተናገሩ

67

ጎንደር ጥር 6/2013 (ኢዜአ) የቀደምት ጀግኖች አባቶች የተጋድሎ ጀግንነት ታሪክ ከመዘከር ባለፈ መልካም እሴቶቻቸውን ማስቀጠል እንደሚገባ የጎንደርና ደባርቅ ዩኒቨርሲቲዎች ምሁራን ተናገሩ፡፡

ዝክረ አጼ ቴዎድሮስ 202ኛ ዓመት የልደት በዓል በጎንደር ከተማ በተለያዩ የኪነ-ጥበባት ዝግጅት ዛሬ ታስቧል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር ዶክተር አማረ ገብሬ በመታሰቢያ ሥነ-ሥርዓቱ ወቅት  እንዳሉት፤ በዘመን ሂደት ያለፉ ጀግኖችን ማሰብ ተገቢ ቢሆንም ሕያው የሆነውን መልካም ተግባራቸውን ማስቀጠል ይገባል፡፡

አጼ ቴዎድሮስ ለኢትዮጵያ አንድነት ያደረጉት ተጋድሎ በታሪክ ጉልህ ስፍራ እንዳለው ጠቅሰው፤ የዛሬይቱን ኢትዮጵያ አንድነቷን አስጠብቆ በማስቀጠል በኩል ትውልዱ ታላቅ አደራና ሃላፊነት አለበት ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ አንድነቷንና ሉአላዊነቷን አስጠብቃ ዘመናትን የዘለቀችው በትውልድ ቅብብሎሽ በተፈጠረ የታሪክ ሰሪነት ተጋድሎ እንደሆነ ዶክተር አማረ አስረድተዋል።

ቀደምት ታሪክ የሰሩ ጀግኖች አባቶቻችንን የአንድ ብሄርና አንድ አካባቢ ትውልድ አድርጎ የማየቱ የተሳሳተ የታሪክ ትርክት ኢትዮጵያዊ አንድነትን የሚሸረሽር በመሆኑ ተገቢነት እንደሌለው ገልጸዋል።

አጼ ቴዎድሮስ ላለፉት 200 ዓመታት  ሲዘከሩ የኖሩት ለውጭ ወራሪዎች ባለመንበርከክና የኢትዮጵያን ሉአላዊ የግዛት አንድነት አስከብረው በማለፋቸው ነው ያለው ደግሞ የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ መምህር ሸጋው ተሰማ ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ የበርካታ ታሪክ ባለቤቶችና የጀግኖች መፍለቂያ ሀገር መሆኗን አመልክተው  ዘመናዊ ትምህርት ሳይኖራቸው ሀገር ያቀኑ ባለውለታ በመሆናቸው ትውልዱ  ሊማርባቸው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የቀደምት አባቶችን መልካም እሴቶችን ማስቀጠል የዚህ ትውልድ የህልውናው መሰረት በመሆኑ ከምንግዜውም በተለየ ኢትዮጵያውያን አንድነታችንን የምናጠናክርበት ጊዜ ነው ብለዋል፡፡

የጎንደር ከተማ ከንቲባ አቶ ሞላ መልካሙ በበኩላቸው አጼ ቴዎድሮስ በዘመነ መሳፍንት ወቅት ኢትዮጵያን ለመከፋፋል የተሰለፉ ሃይሎችን በመመከት አንድነቷን ያስቀጠሉ  ታላቅ መሪ እንደነበሩ አውስተዋል፡፡

በዘር፣ ሃይማኖትና ብሄር መከፋፋልን በማስቀረት ዜጎች በሀገራቸው ኮርተው የሚኖሩባትን ኢትዮጵያን  ለመገንባት የአጼ ቴዎድሮስን አሻራ ማስቀጠል አማራጭ የለውም ሲሉም ገልጸዋል፡፡

በጎንደር ከተማ ፒያሳ አካባቢ በቆመው የአጼ ቴዎድሮስ  ሃውልት ስር የሻማ  ማብራትና  የአበባ  ጉንጉን የማስቀመጥ ሥነ -ሥርዓት እንዲሁም አጼ ቴዎድሮስን  የሚዘክሩ  የሀገር ባህል ውዝዋዜዎችና ግጥሞችም ቀርበዋል፡፡

በመታሰቢያ ሥነ -ሥርዓቱ  የከተማዋ አመራሮች፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ  ፕሬዚዳንት፣  ጀግኖች አርበኞችና የአካባቢው ነዋሪዎች ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም