በኦነግ ሸኔ ላይ እየተወሰደ ባለው እርምጃ የህዝቡ ትብብር እና ድጋፍ ከፍተኛ ነው - የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን

84

አዲስ አበባ ጥር 6/2013 (ኢዜአ) በኦነግ ሸኔ ላይ እየተወሰደ ባለው እርምጃ የህዝቡ ትብብር እና ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል አራርሳ መርዳሣ ገለጹ፡፡

የክልሉ የፖሊስ ሃይል ከአገር መከላከያ እና ከፌዴራል ፖሊስ ጋር በመቀናጀት በህገ ወጡ ቡድኑ ላይ የተጠናከረ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ኮሚሽነር ጀነራል አራርሳ ገለፃ ባለፉት ስድስት ወራት በክልሉ የኦነግ ሽኔን የጥፋት ሃይል ለመቆጣጠር ጠንካራ የህግ ማስከበር ስራ ተከናውኗል ።

በዚህም በክልሉ የተሻለ ሰላም እንዲኖር ማድረግ መቻሉን ገልጸው አሁንም በአንዳንድ ዞኖች እና ወረዳዎች ላይ የታጠቀ የኦነግ ሸኔ እንቅስቃሴ በመኖሩ እርምጃው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የኦነግ ሸኔ ታጣቂ ሃይል ባለፉት ሁለት ዓመታት በህዝቡ ላይ የወሰደው አረመኔያዊ ጥቃት ባለፉት 40 ዓመታት ጨካኝ የሚባሉ መንግስታት በኦሮሞ ህዝብ ላይ ከወሰዱት እርምጃ በላይ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

ህዝቡም የቡድኑን የጭካኔ ተግባር በመቃወም በተለያዩ አካባቢዎች  በሰላማዊ ሰልፍ ጭምር በማውገዝ ላይ መሆኑን ኮሚሽነር ጀነራሉ ጠቅሰዋል።

የፀጥታ ሃይሉ በጥፋት ቡድኑ ላይ እየወሰደ ባለው እርምጃ የክልሉ ህዝብ እያደረገ ያለው ትብብር እና ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑንም ገልጸዋል።

"ኦነግ ሸኔ ካልጠፋ ህዝቡ የሚፈልገውን ዴሞክራሲ እውን ማድረግ አይችልም" ያሉት ኮሚሽነር ጀነራል አራርሳ የቡድኑ ደጋፊ የሆነው የህወሓት ጁንታ መወገዱ ለዚህ ቡድን መጥፋትም አስተዋጽኦው ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡

ጁንታው እንደተደመሰሰ እና በቁጥጥር ስር እንደዋለው ሁሉ ኦነግ ሸኔም የሚያበቃለት የሆናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም