አርብቶ አደሮችን ተጠቃሚ ማድረግ የሚቻለው ከአርብቶ አደሮቹ ችግርና ሀገር በቀል እውቀት የሚነሳ ፖሊሲ በመተግበር ነው ... የዘርፉ ምሁራን

94

አዲስ አበባ፤ ጥር 6/2013(ኢዜአ)በኢትዮጵያ አርብቶ አደሮችን ተጠቃሚ ማድረግ የሚቻለው ከአርብቶ አደሮቹ ችግርና ሀገር በቀል እውቀት የሚነሳ ፖሊሲ በመተግበር መሆኑን የዘርፉ ምሁራን ተናገሩ።

የግብርና ሚኒስቴር በበኩሉ እስከ ቀበሌ ድረስ ያሉ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የፖሊሲ ክለሳ እያደረገ መሆኑን አስታውቋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የሚዘጋጀው 'አዲስ ወግ' የውይይት መድረክ 'የቆላማ አካባቢዎች የአርብቶ አደሮች የልማት ጉዞ' በሚል ርእሰ ጉዳይ ላይ ዛሬ ምክክር አድርጓል።

በመድረኩ በአርብቶ አደር አከባቢዎች የሚሰሩ ኤክስፐርቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተሳተፉ ሲሆን፤  በነዚህ አካባቢዎች የተተገበሩ የልማት ፖሊሲዎች ያስገኙት ውጤትና ያጋጠሙ ክፍተቶች ላይ ውይይት ተደርጓል።

በመድረኩ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሴ፤ የሱማሌ ክልል የመስኖና ተፋሰስ ልማት ቢሮ ሃላፊ አብዱረህማን ኢድ እና የአርብቶ አደር ጉዳይ ኤክስፐርት የሆኑት ሃኒ ሃሰን የውይይት የመነሻ ሃሳብ አቅርበዋል።

ወይዘሮ ሃኒ ሃሰን በዚህን ወቅት የአርብቶ አደር አከባቢዎች ከኢትዮጵያ አጠቃላይ ስፋት 60 በመቶው የሚሆነው እንደሚሸፍኑ ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ ከዚህ ቀደም አርብቶ አደሮችን በሚመለከት የሚተገበረው ፖሊሲ 'በእኔ አውቅልሃለሁ መንፈስ' ከላይ ወደ ታች የሚተገበር በመሆኑ ለውጥ እንዳላመጣ አስረድተዋል።

በዚህ የተነሳም ኢትዮጵያ ከአርብቶ አደር አከባቢዎች ማግኘት የሚገባትን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንዳላገኘች አብራርተዋል።

በተለይ አርብቶ አደሮች በሀገሪቱ ጠረፋማ አካባቢዎች የሚኖሩ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ጥቂት የማይባል ሀብት ከሀገር ውጭ እንዲወጣ አድርጓል ነው ያሉት።

የሱማሌ ክልል የመስኖና ተፋሰስ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ አብዱረህማን ኢድ፤ ባለፉት 15 ዓመታት የአርብቶ አደር ተጠቃሚነት የሚለካው ምን ያህል አርብቶ አደር በመንደር ተሰባሰበ በሚለው ሃሳብ ብቻ እንደነበር ነው ያነሱት።

'የግብርና እና የገጠር ልማት' በሚል የተቀረጸው ፖሊሲ የበርካታ ተቋማትን ቅንጅት የሚጠይቅ ሆኖ መቀረጹን አንስተው፤ ተቋማቱ በሚገባ መናበብ ባለመቻላቸው የሚፈለገውን ለውጥ እንዳላመጣ ገልጸዋል።

አሁን ላይ አርብቶ አደሩን በሚመለከት የተሻለ ቅንጅታዊ አሰራርና ትኩረት መኖሩንም ነው የገለጹት።

የውይይቱ ተሳተፊዎች በዘርፉ መስተካከል አለባቸው ያሏቸውን ነጥቦች አንስተዋል።

በተለይ አርብቶ አደሩን ተደራሽ ያደረገ የፋይናንስ ስርዓት መዘርጋት ይኖርበታል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋለ።

በፖሊሲና ፕሮግራም ቀረጻ ወቅት የአርብቶ አደሩን እውቀት መጠቀም ወሳኝና አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ያሉ ስመጥር የዘርፉ ባለሙያዎችን ባሳተፈ መልኩ በአርብቶ አደር አካባቢዎች ላይ የሚተገበር የፖሊሲ ክለሳ እየተደረገ መሆኑን ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሴ ተናግረዋል።

በክለሳው ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ ያሉ ባለደርሻ አካላት ተሳታፊ እንደሆኑም ነው ያነሱት።

የፖሊሲ ክለሳው ለአርብቶ አደሩና አርሶ አደሩ ብድርና ኢንሹራንስ የሚሰጥ የግብርና ባንክ እስከማቋቋም የሚደረስ እቅድ መያዙንም ጨምረው  ገልጸዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የሚዘጋጀው የ 'አዲስ ወግ' የውይይት መድረክ በዋናነት በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ላይ የውይይት ባህልን በማዳበር ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ ሃሳቦችን ማሰባሰብ ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑ ይታወቃል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም