ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከኦስትሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ተወያዩ

104

አዲስ አበባ፤ ጥር 6/2013(ኢዜአ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከኦስትሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሌክሳንደር ሻለንበርግ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያዩ።

ውይይቱን የተከታተሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ የሁለቱ አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መክረዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ለኦስትሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሌክሳንደር ሻለንበርግ በህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር፣ የኢትዮ- ሱዳን የድንበር ጉዳይና በትግራይ ክልል ስለነበረው አጠቃላይ የህግ ማስከበር ሂደት ገለፃ አድርገውላቸዋል።

የኦስትሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሌክሳንደር ሻለንበርግ በበኩላቸው የኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን የህዳሴ ግደብ የሶሰትዮሽ ድርድር ሁሉንም ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል።የኢትዮ- ሱዳን ወቅታዊ የድንበር አካባቢ ችግርም በውይይት እና በድርድር መፈታት ይኖርበታል ነው ያሉት።

መንግስት በትግራይ ክልል ያካሄደው ህግ የማስከበር ዘመቻም በአጭር ጊዜ በውጤታማነት በመጠናቀቁ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያና ኦስትሪያ በግብርና፣ ኢነርጂና ሌሎችም መስኮች የተጠናከረ ትብብር እንዳላቸው አስታውሰው፤ በንግድና ኢንቨስትመንትም ግንኙነታቸውን ለማጠናከር መንግስታቸው ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋለ።

የኦስትሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሻለንበርግ በኢትዮጵያ የሁለት ቀናት የስራ ጉብኝት የሚያደርጉ ሲሆን ከሌሎች የኢፌዴሪ ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች ጋር ውይይት እንደሚያደርጉም ይጠበቃል።

የኦስትሪያ መራህይ መንግስት ሰባስቲያን ኩርዝ ከሁለት ዓመት በፊት በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ማድርጋቸው ይታወሳል።የኢትዮጵያና ኦስትሪያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተጀመረው እኤእ በ1905 መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም