ቀዳማዊት እመቤት ለአካል ጉዳተኞች ዊልቸርና የብሬል ኮምፒውተሮችን በድጋፍ አበረከቱ

71

ጎንደር፤ ጥር 6/2013 (ኢዜአ) ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው በጎንደር ከተማ ለሚገኙ አካል ጉዳተኞች 48 ዊልቸሮችና አምስት የብሬል መጻፊያ ኮምፒውተሮችን በድጋፍ አበረከቱ፡፡

ድጋፉ የተደረገላቸው በከተማው በስድስት ክፍለ ከተሞች ውስጥ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚተዳደሩ 53 አካል ጉዳተኞች ነው።

የጎንደር ከተማ ከንቲባ አቶ ሞላ መልካሙ በድጋፍ አሰጣጥ ስነ-ስርአት ላይ እንደገለጹት የቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት በከተማው በትምህርት መስክ በርካታ ድጋፎችን ሲያደርግ ቆይቷል።

የሎዛ ማርያም 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን ገንብቶ ከማስረከብ ጀምሮ በጻዲቁ ዮሃንስ ትምህርት ቤት ለሚገኙ አካል ጉዳተኞች የትምህርት መርጃ መሳሪያዎችን በመደገፍ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር በበኩላቸው "የቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት በሁሉም ክልሎች ትምህርት ቤቶችን ገንብቶ በማስረከብ ግንባር ቀደም ድርሻ አለው "ብለዋል፡፡

በጎንደር ከተማም ለአካል ጉዳተኞችና አይነስወራን ተማሪዎች ለተደረገው  ድጋፍ  ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ድጋፉ ከተደረገላቸው መካከል በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የ2ኛ አመት የማኔጅመንት ተማሪ የሆነውና በእግሩ ላይ በደረሰበት አደጋ ለአካል ጉዳት የተዳረገው ተማሪ  አብርሃ  ደረበ  አንዱ ነው፡፡

በቀዳማዊት እመቤት የተደረገለት የዊልቸር ድጋፍ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን በሚገባ ተከታትሎ ለመመረቅ የሚያግዘው መሆኑን ተናግሯል፡፡

ጥጥ ፈትላ ልጆችዋን እንደምታስተዳድር የተናገረችው በከተማው የሳሙና በር ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ አስናቁ አበበ "የተደረገልኝ የዊልቸር ድጋፍ ተንቀሳቅሼ በመስራት ኑሮዬን ለማሸነፍ ያስችለኛል" ብላለች፡፡

በድጋፍ አሰጣጥ ስነ-ስርአት ላይ የአማራ ክልል አፈጉባኤ ወይዘሮ ወርቅሰሙ  ማሞን  ጨምሮ የከተማው አመራሮች የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም