በሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ የኢትዮ-ሱዳን የድንበር ልዩነት በሰላማዊ መንገድ መፈታት እንዳለበት አሳሰቡ

67

ጥር 5/2013(ኢዜአ) በሱዳን የኢ.ፌ.ድ.ሪ አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ በኢትዮጵያ እና ሱዳን መካከል ያለው የድንበር ጉዳይ ባሉ የሁለትዮሽ ስምምነቶች እና የጋራ የድንበር መድረኮች አማካኝነት በሰላማዊ መንገድ መፈታት እንዳለባቸው አሳሰቡ።

የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የብሔራዊ ድንበር ኮሚሽን ዛሬ ተቀማጭነታቸው በሱዳን ለሆኑ ዲፕሎማቲክ ሚሽኖች፣ ቆንስላዎች እና የዓለምአቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች አድርገዋል።

አምባሳደር ይበልጣል ከዳግልሽ ተራራ በስተሰሜን ከሰፈራ እና ከእርሻ መሬት ጋር በተያያዘ የተፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት ሁለቱን ሀገራት የሚያስማማ የመፍትሔ ሃሳብ እንዲመጣ የሚደነግገው እና በሁለቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እ.ኤ.አ. ሐምሌ 18 ቀን 1972 የተደረገው የማስታወሻ ልውውጥ ከፍ ያለ ፋይዳ ያለው መሆኑን በአጽንኦት አስረድተዋል።

በ1972ቱ የማስታወሻ ልውውጥ በተቀመጠው መሰረት የጉዊን መስመርን ዳግም ማካለል ከመጀመሩ በፊት ከዳግልሽ ተራራ በስተሰሜን ከእርሻ መሬት እና ሰፈራ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት የጋራ ልዩ ኮሚቴው ሁለቱን ሀገራት የሚያስማማ የመፍትሔ ሃሳብ ያካተተ ሪፖርት ለጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ማቅረብ እንደሚኖርበትም አያይዘው ገልጸዋል።

የጋራ ልዩ ኮሚቴው ሁለቱን ሀገሮች የሚያስማማ የመፍትሔ ሃሳብ ለማቅረብ ስምንት ዙር ስብሰባዎችን ቢያካሂድም ኃላፊነቱን ገና እንዳላጠናቀቀ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ-ሱዳን ድንበር የጋራ ልዩ ኮሚቴ ስራ ባልተጠናቀቀበት ሁኔታ እና የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በጥቅምት ወር መጨረሻ ህግ ለማስከበር ወደ ትግራይ ክልል ያደረገውን ስምሪት እንደ መልካም አጋጣሚ መጠቀሙን አምባሳደር ይበልጣል እንስተዋል።

በዚህም የሱዳን ሰራዊት ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ዘልቆ በመግባት ንብረት ከመዝረፉ፣ ወታደራዊ እና የእርሻ ካምፖችን ከማቃጠሉ ባሻገር በኢትዮጵያውያን ላይ እስራት፣ ጥቃት እና ግድያ መፈጸሙ እንዲሁም በሺ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ማፈናቀሉን ጠቅሰው ፤ይህ የ1972 የማስታወሻ ልውውጥን በግልጽ የጣሰ ተግባር መሆኑን አስረድተዋል።

አምባሳደሩ አክለውም በሁለቱ እህትማማች ሀገራት ጸንቶ ከቆየው አጋርነት እና ትብብር መንፈስ በተቃረነ መልኩ የሱዳን ሰራዊት አጋጣሚውን በመጠቀም የኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ ሰራዊት ለቋቸው የወጣ ካምፖችን መቆጣጠሩን ገልጸዋል።

ሱዳን በችግር ውስጥ በነበረችበት ጊዜ ሁሉ ኢትዮጵያ ከሱዳን ህዝብ ጎን መቆሟን ያስታወሱት አምባሳደር ይበልጣል፤ ኢትዮጵያ በውስጥ ጉዳይዋ በተጠመደችበት ወቅት ከሱዳን ሰራዊት የደረሰባት ጥቃት የሚገባት አልነበረም ብለዋል።

አምባሳደሩ እንዳሉት የማስተካከያ እርምጃ በፍጥነት ካልተወሰደ፣ ታይቶ የማይታወቀው የሱዳን ሰራዊት ተግባር የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ብሎም የጋራ ድንበሩን ዳግም የማካለሉን ስራ የሚያወሳስብ እና ለሁለቱ ሀገራት ህዝቦች እንዲሁም ለቀጠናው ከፍ ያለ አሉታዊ ተጽዕኖ ይኖረዋል።

የኢትዮጵያ እና ሱዳን የድንበር ልዩነቱን ሁለቱ ሀገራት በገቧቸው ስምምነቶች እና ባሉ የጋራ የድንበር መድረኮች መሰረት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ኢትዮጵያ ቁርጠኛ መሆኗንም አረጋግጠዋል።

ለችግሩ ዘላቂ እልባት ለመስጠት፡

አንደኛ፣ የሱዳን ሰራዊት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የፈጸመውን ወረራ በመቀልበስ በ1972ቱ የማስታወሻ ልውውጥ በተቀመጠው መሰረት ወደ ቅድመ-ኖቬምበር 2020 (እ.ኤ.አ.) እንዲመለስ፣

ሁለተኛ፣ ወደ ድንበር ዳግም ማካለል ከመገባቱ በፊት የጋራ ልዩ ኮሚቴው በ1972 የማስታወሻ ልውውጥ መሰረት ከዳግሊሽ ተራራ በስተሰሜን ከሰፈራ እና እርሻ መሬት ጋር በተያያዘ የተፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት ሁለቱን ሀገራት የሚያስማማ የመፍትሔ ሃሳብ የማቅረብ ስራውን እንዲያጠናቅቅ፣

ሶስተኛ፣ የጋራ ድንበሩን ዳግም ለማካለል ሁለቱ ሀገራት ያቋቋሟቸው የጋራ የድንበር ኮሚሽን፣ የጋራ የቴክኒክ የድንበር ኮሚቴ፣ እና የጋራ ልዩ ኮሚቴ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ እና ስራቸውን እንዲያጠናቅቁ ማድረግ ተገቢ እንደሆነ አጽንኦት መስጠታቸውን በሱዳን ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም