ህዝብን በሚያገለግሉ ተቋማት መካከል ህግን የተከተለ ቅንጅታዊ አሰራር እንዲጎለብት ድጋፍ ይደረጋል- ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ

95

አዲስ አበባ፣ ጥር 4/2013 (ኢዜአ) ህዝብን በሚያገለግሉ ተቋማት መካከል ህግን የተከተለ ቅንጅታዊ አሰራር እንዲጎለብት የሚጠበቅበትን ድጋፍ እንደሚያደርግ የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አስታወቀ። 

በጠቅላይ ዐቃቤ ህግና በፌደራል ተቋማት መካከል በሚኖረው ቅንጅታው አሰራር ላይ ትኩረቱን ያደረገ ውይይት ተካሄዷል።

በውይይቱ ረቂቅ መመሪያዎች ሲወጡ ግብዓት የሚሆኑ ሀሳቦችን በምን መልኩ ማሰባሰብ እንደሚቻል ምክክር ተደርጓል። 

የፌደራል ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አቶ ተስፋዬ ዳባ እንደተናገሩት ውይይቱ በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ እና በፌደራል ተቋማት መካከል የሚኖረውን ቅንጅታዊ አሰራር በሚመለከት ግንዛቤ የሚፈጠርበት ነው።

ኢትዮጵያ እያስመዘገበችው ያለውን የኢኮኖሚ እድገት ተከትሎ የሀገር ውስጥ ተቋማት ከውጭ ኩባንያዎች ጋር የሚፈጥሩት መስተጋብር መጨመሩንም ተናግረዋል።

ይህም የፍትሐብሄር ጉዳዮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከቱ እንዲመጡ አድርጓልም ነው ያሉት። 

የፍትሃብሔር ጉዳይ ህግን መሰረት አድርጎ መመራት ካልተቻለ ተቋማት ጊዜያቸውን አላስፈላጊ በሆኑ ክርክሮች በማሳለፍ የተቋቋሙለትን ዓላማ በአግባቡ እንዳያሳኩ እንቅፋት እንደሚፈጥርም አብራርተዋል።

በዚህ ሂደት ዋነኛዎቹ ተጎጂዎች ህዝብና መንግስት መሆናቸውን በመጠቆም።

በመሆኑም የሚኖራቸው መስተጋብር ህግን መሰረት ያደረገ እንዲሆን የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የሚጠበቅበትን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በተለይ ውሎች፣ ድርድሮች እና ክርክሮችን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ድጋፍ ያደርጋል ሲሉም አረጋግጠዋል።

ይህ እንዲሳካ ደግሞ ሁሉም ተቋማት የሚጠበቅባቸውን ሚና ለመወጣት ዝግጁ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ የፌደራል ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አቶ ተስፋዬ ዳባን ጨምሮ ሚኒስትር ዴኤታዎች እና የፌደራል ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም