በምዕራብ ሸዋ 32 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት በመስኖ ለማ

84

አምቦ፣ ጥር 4/2013(ኢዜአ) በምዕራብ ሸዋ ዞን እስካሁን ባለው የበጋ ወቅት 32 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት በመስኖ መልማቱን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የዞኑ እርሻና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት የመስኖ ልማት ባለሙያ አቶ ገዛኸኝ ዲንሳ ለኢዜአ እንደገለፁት እስካሁን በመስኖ የለማው መሬት በአንደኛው ዙር ይለማል ተብሎ በእቅድ ከተያዘው 34 ሺህ ሄክታር ውስጥ ነው።

እስካሁን ከለማው መሬት ውስጥ 9 ሺህ 507 ሄክታሩ ለመጀመሪያ ጊዜ በስንዴ ዘር የተሸፈነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የጓሮ አትክልትና በቆሎ ደግሞ ልማቱ በዋናነት ያተኮረባቸው መሆኑን ጠቅሰዋል።

የመስኖ ልማቱ በዘመናዊና በባህላዊ መንገድ ወንዞችን በመጥለፍ፣ በግድቦችና የውሃ መሳቢያ ሞተሮችን በመጠቀም እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በአንደኛ ዙር በመስኖ ከሚለማው አጠቃላይ መሬት ከ1 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ አመላክተዋል፡፡

የደንዲ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር አለማየሁ ቀጄላ  ዘንደሮ ለመጀመሪያ ጊዜ በመስኖ በመታገዝ ግማሽ ሄክታር ማሳቸውን በስንዴ ዘር መሸፈናቸውን ተናግረዋል ።

የወረዳው የግብርና ባለሙያዎች አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረጉላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

"ዘንድሮ በመስኖ በመታገዝ ሽንኩርት፣ ጥቅል ጎመን፣ ቲማቲምና ቃሪያ እያለማሁ ነው" ያሉት ደግሞ የጨሊያ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ቶለሳ ዲባባ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም