በጋምቤላ ክልል ኮሮናን ለመከላከል ክልላዊ የንቅናቄ መረሃ ግብር ተጀመረ

ጋምቤላ፣ ጥር 3/2013(ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል " እንድናገለግልዎ ማስክዎን ያድርጉ" በሚል መሪ ሀሳብ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚያግዝ ክልላዊ የንቅናቄ መረሃ ግብር ዛሬ በይፋ ተጀመረ።

መረሃ ግብሩ ለስድስት ወራት የሚዘልቅ መሆኑ ተገልጿል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ የንቅናቄ መረሃ ግብሩን ሲያስጀምሩ እንዳሉት የስርጭት መጠኑ እያሻቀበ የመጣውን የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል መላው የክልሉ ህዝብና ባለድርሻ አካላት ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል።

የኮሮና ቫይረስ እንደ ሀገር ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ በክልሉ ብሎም በሀገሪቱ በተቀየሰው የመከላከል ዘመቻ በሁሉም መዋቅሮች ሰፊ ስራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

ሆኖም የቫይረሱ ስርጭት እየተስፋፋ ባለበት ሁኔታ በማህበረሰቡም ሆኑ አመራሩ ዘንድ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብልን ጨምሮ ሌሎችም ቫይረሱን ለመከላከል የወጡ መመሪያዎች ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ መዘናጋት መኖሩን ተናግረዋል።

በተለይም ህዝብ በሚበዛባቸው የሰርግ፣ ለቅሶ ፣ ሥልጠና እና መዝናኛ ቦታዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ያለመጠቀምና ሌሎች ክልከላዎችንም ተግባራዊ ያለማድረግ ችግሮች እንደሚስተዋሉ ጠቅሰዋል።

መላው የክልሉ ማህበረሰብና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የቫይረሱ ስርጭት አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን በመገንዘብ ወረርሽኙን ለመከላከል በመንግስት የተላለፉ መመሪያዎችን ገቢራዊ ሊያደርጉ እንደሚገባ አሳስበዋል።

’’እንድናገለግልዎ ማስክዎን ያድርጉ’’ በሚል መሪ ሃሳብ ይፋ ዛሬ ለሆነው ክልላዊ የንቅናቄ መረሃ ግብር ውጤታማ ለማድረግ የመንግስት፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት በቁርጠኝነት መስራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሮት ጋርዊች በበኩላቸው በክልሉ ቀደም ሲል የኮሮና ቫይረሱ በመከላከል ረገድ በማህበረቡ ዘንድ የተሻለ ተነሳሽነት እንደነበረ አስታውሰዋል።

አሁን ላይ ግን በማህበረሰቡ ዘንድ በተለይም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብልን ከመጠቀም ጀምሮ ሌሎች ክልከላዎች ላይ ከፍተኛ መዘናጋት መኖሩን ተናግረዋል።

ዛሬ የተጀመረው የንቅናቄ መረሃ ግብር ዓላማም በማህበረሰቡ አካባቢ የሚታዩ የመዘናጋት ችግር ለማቃለል መሆኑን ገልጸው የንቅናቄ መረሃ ግብሩ ለቀጣዮቹ ስድስት ወራት የሚተገበር ነው ብለዋል።

’’እንድናገለግልዎ ማስክዎን ያድርጉ’’ የሚለው አስገዳጅ መመሪያም ከጥር 4 ቀን 2013ዓ.ም. ጀምሮ በሁሉም የመንግስት፣ መንግስታዊ ያልሆኑና የግል ተቋማት ተግባራዊ እንደሚሆንም ተገልጿል።

በንቅናቄ ማስጀመሪያ መረሃ ግብሩ ላይ የምክር ቤት አባላትን ጨምሮ የክልል፣ ዞን፣ ወረዳ አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም