በመኸር እርሻ ከለማው ሠብል በዘጠኝ ሚሊዮን ሄክታር ላይ የነበረው ተሰብስቧል .... ግብርና ሚኒስቴር

121

አዲስ አበባ፤ ጥር 3/2013(ኢዜአ) ባለፈው መኸር በ13 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ከለማው ሠብል በዘጠኝ ሚሊዮን ሄክታር ላይ የነበረው መሰብሰቡን ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሚኒስቴሩ የሠብል ልማት ዳይሬክተር አቶ ኢሳያስ ለማ ለኢዜአ እንደተናገሩት በ2012/2013 የመኸር እርሻ በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች 13 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በሰብል ተሸፍኗል።

ከዚሁ ውስጥ በዘጠኝ ሚሊዮን ሄክታር ላይ የነበረው ሠብል መሰብሰቡን የገለጹት ዳይሬክተሩ 'በትግራይ ክልል ምርት ቢሰበሰብም የተቀናጀ መረጃ ባለመኖሩ በአሃዙ አልተካተተም' ብለዋል።

በመኸር እርሻ ከዕቅድ በላይ መታረሱን ገልጸው በአገሪቷ አብዛኛው ምርት መሰብሰቡንና የቀረው ከ15 በመቶ በታች መሆኑን ተናግረዋል።

በመኸር እርሻ ከ16 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ተዘጋጅቶ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ኢሳያስ፤ 80 በመቶው ጥቅም ላይ መዋሉንና ቀሪው ለመስኖና ለበልግ እርሻ እንደሚውል ገልፀዋል።

ለመኸር እርሻ ከ700 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሮች መቅረቡንና እንደ አፈሩ ተስማሚነት ከአምስት አይነት በላይ የአፈር ማዳበሪያ ጥቅም ላይ መዋሉንም ተናግረዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ኮሮናቫይረስ፣ የጎርፍ አደጋና የአንበጣ መንጋ በሠብል ምርት ላይ በቤተሰብ ደረጃ የተወሰነ ተጽዕኖ ቢያስከትልም በአገር ደረጃ ለማግኘት በታቀደው ምርት ላይ ተጽዕኖ አላደረሰም።

"ከበቂ በላይ ዝናብ መጣሉ፣ ለአርሶ አደሮች የሚፈለገው ስልጠናና ግብዓት በወቅቱ መሰጠቱ ከሚፈለገው በላይ ምርት ለማግኘት አስችሏልም" ብለዋል።

ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ  እንዲቻል ከ3 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በአገር አቀፍ ደረጃ በኩታ ገጠም እርሻ እንዲለማ መደረጉንም ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት።

በመኸር እርሻው እንደ አገር ከአንድ ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በትራክተር መታረሱንም አቶ ኢሳያስ ለኢዜአ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም