ብልጽግና ፓርቲ ፈተናዎችን በማለፍ አገር የማዳን ተግባር ማከናወን ችሏል

92

ጥር 2/2013 (ኢዜአ)  ብልጽግና ፓርቲ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ በማለፍና ፈተናዎችን በመቋቋም አገር የማዳን ስራዎችን ማከናወን መቻሉን በአዲስ አበባ የፓርቲው ጽህፈት ቤት ኃላፊ ገለጹ።

የቦሌ ክፍለ ከተማ ኮሙኒኬሽን አነስተኛ የሬዴዮ ፕሮዳክሽን ስቱዲዮና የክፍለ ከተማው የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ምረቃ ተከናውኗል።

የከተማዋ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መለሰ አለሙ "ፓርቲው ሁሉንም ኢትዮጵያዊያን በእኩል በማገልገልና የሚያጋጥሙትን ፈተናዎች በብቃት በማለፍ ላይ ይገኛል" ሲሉ ተናግረዋል።

ፓርቲው በአገሪቷ እየተተገበረ ያለውን ለውጥ በብቃት የመምራት ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ጠቅሰው የመንግስትና የፓርቲ ሚና መደበላለቅን ለማስቀረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

የፓርቲና የመንግስት ስራን በመለየት ሁለቱ አካላት ተቋማዊና መንግስታዊ ቁመና እንዲኖራቸው ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

ፓርቲው አገሪቷን ወደፊት ለማራመድ የሚያስችል ተስፋና ዕድል እንድንሰንቅ አድርጎናል ያሉት ኃላፊው የሚያጋጥሙትን ፈተናዎችና ድክመቶች እያለፈና እያረመ ወደፊት መጓዝ የሚችል መሆኑን በተጨባጭ ማሳየት ችሏል ነው ያሉት።

በዋናነትም ፓርቲው አገርና ሕዝብን ወደፊት የሚያሻግርና የሚያገለገል መሆኑን አክለዋል።

ከቀደመው አካሄድ ትምህርት በመውሰድ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን የሚያገለግል የተለየ አስተሳሰብ ይዞ የመጣ ፓርቲ መሆኑንም አውስተዋል።

ፓርቲው የነበሩትን ክፍተቶች በማረም የላቀ ስራ እንደሚጠበቅበትና ቀጣዩ አገራዊ ምርጫ ስኬታማ እንዲሆንም የፓርቲው አባላት ሚና ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።

የቦሌ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መኮንን አምባዬ የፓርቲውን ጽህፈት ቤት ተደራሽነት በሁሉም ወረዳዎች ለማስፋት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

ከጽህፈት ቤት ግንባታ በተጨማሪ በአባላት የአቅም ግንባታ ስራ ላይ ትኩረት ይደረጋል ነው ያሉት።

ከሬዴዮ ፕሮዳክሽን በተጨማሪ በቀጣይ የቦሌ ክፍለ ከተማ ሕዝብ ድምጽ የሚሆን፣ ችግሮቹን ማስተጋባትና መፍታት የሚያስችል የማኅበረሰብ አቀፍ ሬዴዮ ይቋቋማልም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም