በመተከል ዞን የተፈጠረውን የፀጥታ ችግር ከመሰረቱ ለመፍታት ሰፊ ስራ ይጠይቃል

82

አዲስ አበባ ጥር 2/2013 (ኢዜአ) በመተከል ዞን የተፈጠረውን የፀጥታ ችግር ከመሰረቱ ለመፍታት በአመለካከት ላይ ሰፊ ስራ መስራት እንደሚያስፈልግ የአካባቢው ነዋሪዎች አሳሰቡ።

በፌዴራል መንግስት ተቋቁሞ የሕግ የበላይነት በማስከበር ላይ የሚገኘው ግብረ ኃይል ከመተከል ዞን ምሑራን ጋር ተወያይቷል።

በዞኑ ለተፈጠረው ችግር ዘርፈ ብዙ ምክንያቶች መኖራቸውን ያነሱት ምሑራኑ በዋናነት ግን የወጣቱ አመለካከት በጥፋት ሃይሎች መመረዝ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ለዚህ ደግሞ በማኅበራዊ ድረ ገፆች፣ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃንና በአመራሮች ሳይቀር አንድን ወገን የሚደግፉ፣ ሕዝብን ከሕዝብ፣ ብሄርን ከብሄር የሚያጋጩ መልዕክቶች አሁንም ድረስ እየተላለፉ መሆኑን ጠቁመዋል።

በነበረው ሁኔታ በተለያዩ አካላት የጥፋት መልዕክቶች ሲተላለፉና የማኅበረሰቡ አመለካከት ሲመረዝ ሃላፊነቱን የተወጣ አካል አለመኖሩንም አንስተዋል።

ችግሩን ከመሰረቱ ለመፍታት በመተከል ዞን የሚኖሩና መላው ኢትዮጵያዊያን እንደ ኢትዮጵያዊ ማሰብ እንዳለባቸው አመልክተዋል።

በዞኑ አንድ ዜጋ ሲጎዳ በብሄሩ ሳይሆን ሰው በመሆኑ ብቻ የሚያዝን ማኅበረሰብ ካልተፈጠረና ሕገወጥ እንቅስቃሴዎችን በአንድ ላይ የሚታገል ማኅበረሰብ ካልተፈጠረ ችግሩ ሊቀጥል እንደሚችል ጠቁመዋል።

ሰውን በሰውነቱ ብቻ የሚመዝንና በእኩል የሚያይ ዜጋ የመፍጠር ጉዳይ የሁሉም ሃላፊነት መሆኑንም ተናግረዋል።

በዚህ ረገድ በተለይ መገናኛ ብዙሃን፣ የሠብዓዊ መብት ተቋማትና ተሟጋቾች እንዲሁም ሌሎች ገለልተኛ አካላት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው መስራት ሲገባቸው "ዘንግተውታል" ነው ያሉት ምሑራኑ።

በተለይ የመተከልን ሠላም ማጣት በተመለከተ አንዳንድ የማኅበራዊ አንቂዎች፣ ሃላፊነት የጎደላቸው አመራሮችና መገናኛ ብዙሃን ወገንተኛና አድሏዊ የሆኑ ችግሩን የሚያባብሱ መመረጃዎችን እያሰራጩ መሆኑን ተናግረዋል።

በዞኑ ለተፈጠረው ችግር መፍትሄ አመላካችና ሚዛናዊ ስራ ነው የሚያስፈልገው ነው ያሉት ምሁራኑ መንግስት ከዚህ የወጡ አካሄዶችን እያየ የእርምት እርምጃ እንዲወስድም ጠይቀዋል።

ውይይቱን የመሩት የኮማንድ ፖስቱን የፀጥታ ሃይል በበላይነት የሚመሩት ሌተናል ጄኔራል አስራት ዴኔሮ በበኩላቸው ችግሩ ሆን ተብሎና ለ30 ዓመታት ታስቦበት የተሰራ መሆኑን ግብረ ሃይሉ ከዞኑ ነዋሪዎች ጋር ባካሄዳቸው ውይይቶች መገንዘቡን ተናግረዋል።

ይህን መፍታት የሚቻለው መንግስት እንደ መንግስት የሚሰራቸው ስራዎች እንዳሉ ሆነው ምሑራንን ጨምሮ ሁሉም ዜጋ በአንድነት ላይ በመስራት ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም