ሀገራዊ የብልጽግና ጉዞን እውን ለማድረግ የወጣቱ ሚና የላቀ ነው

53

ጋምቤላ ጥር 2/2013 (ኢዜአ) ሀገራዊ የብልጽግና ጉዞን እውን ለማድረግ የወጣቱ ሚና የላቀ መሆኑን የጋምቤላ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የክልሉ የብልጽግና ወጣቶች ሊግ የውይይት መድረክ ትላንት ተካሄዷል።

የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፋት ቤት ኃላፊ አቶ ላክደር ላክባክ እንደገለጹት በሀገሪቱ እየተካሄደ ያለውን ሁለንተናዊ ለውጥና የብልፅግና ጉዞ እውን ለማድረግ ወጣቱ ኃይል የማይተካ  ሚና አለው።

የክልሉን ብሎም የሀገሪቱን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚዊና ፖለቲካዊ እድገት ውጤታማ ማድረግ  የሚቻለው ወጣቱ በልማት፣ በሰላምና በዴሞክራሲ ግንባታ በንቃት መሳተፍ ሲችል መሆኑን ተናግረዋል።

ከለውጡ በፊት ወጣቱ በሁሉም ዘርፎች የድርሻውን እንዳይወጣ እድል በመነፈጉ ምክንያት ከነበረው መንግስትና ፓርቲ ጋር መተማመንና መከባበር ያልተቻለበት ጊዜ እንደነበር አስታውሰዋል።

"ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ቀደም ሲል የነበረው ኢ-መደበኛ አደረጃጀት ወደ መደበኛነት ተቀይሮ ወጣቶችና ሴቶች ወደ ስራ በመግተቻው በሰላምና በዴሞክራሲ ግንባታ  የድርሻቸውን እየተወጡ ነው" ብለዋል።

ለሰላም፣ ለልማትና ለዴመክራሲ ግንባታ ስራዎች ውጤታማነት በወጣቶች የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አሳስበዋል።

"በመንግስትም ሆነ በፓርቲው የተጀመረው ሁለንተናዊ ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል" ብለዋል።

የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ሰብሳቢ ወጣት ሯች ጎች  በበኩሉ ከአሁን በፊት በነበረው የህወሓት የፖለቲካ ሴራ ወጣቱም ሆነ መላው የክልሉ ህዝብ ተጠቃሚ ሳይሆን  መቆየቱን ተናግሯል።

አሁን ላይ ወጣቱም ሆነ የክልሉ ህዝብ ከሴራ ፖለቲካ ተላቆ እኩል ተጠቃሚ የመሆን ድል ባለቤት መሆኑን ጠቁመው "በቀጣይ የሴራ ፖለቲካ አራማጆችን ወጣቱ በዝምታ አይመለከትም" ብሏል።

"ከአሁን በፊት ወጣቱንም ሆነ ሌላውን ህዝብ በጎጥና በመንደር በመከፋፈል አንድነቱን ለመሸርሽር ሲሰራ ነበር" ያለው ደግሞ የሊጉ ምክትል ሰብሳቢ ወጣት ኡጁሉ ቢሩ ነው።

አሁን ላይ ወጣቱም ሆነ ህዝቡ ልዩነቶች እንዳማያስፈልጉ በመረዳቱ በክልሉ ሰላም ሊኖር ችሏል፤ በቀጣይም በሚስማሙና በሚያግባቡ ጎዳዮች ዙሪያ እንሰራለን " ሲል ተናግሯል።

የመድረኩ ተሳታፊ ወጣት ታቫን ጀምስ በሰጠው አስተያየት "ወጣቱ በገንዘብ  እየተታለለ ሀገር ለማጥፋት የሚሞክር ከሆነ እራሱን ጭምር እያጠፋ መሆኑን መገንዘብ አለበት" ብሏል።

ወጣቱ ከዚህ መሰል አስተሳሰብ በመውጣት ለዘንድሮ ምርጫ ሰላማዊ ሂደትና ለተጀመረው የብልጽግና ጉዞ ስኬታማነት የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ መክሯል።

"ወጣቱ ከጽንፈኝነትና ከብሄርተኝነት አስተሳሰቦች በመውጣት መንግስት በጀመራቸው የሰላም፣ የዴምክራሲ ግንባታና የልማት ስራዎች በንቃት ለመሳተፍ ዝግጁ ነው" ያለው ደግሞ ወጣት አሳምነው ተፊሪ ነው።

በመድረኩ ወጣቱ በሀገረ ግንባታ ስላለው ሚና ጹሁፍ ቀርቦ ውይይት የተደረገበት ሲሆን በውይይት መድረኩ ከ350 በላይ ወጣቶች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም