የገዳ ሥርዓትን ለትውልድ እንዲተላለፉ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ

1889

ዲላ፣ ጥር 1 /2013 (ኢዜአ) የገዳ ሥርዓትን በማበልፀግ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፉ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ።

የገዳ ሥርዓት በዓለም ቅርስነት የተመዘገበበትን አራተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ “ሰላም እና አቃፊነት የገዳ ሥርዓት እሴቶቻችን ናቸው!” በሚል መሪ ሀሳብ በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የገዳ ፓናል ውይይት እየተካሄደ ነው።

በውይይቱ መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ጫላ ዋታ የገዳ ስርዓት የኦሮሞ ብቻ ሳይሆን የጥቁር ህዝቦች በተለይም የአፍሪካዊያን ሀገር በቀል እውቀት መሆኑን ገልጸዋል።

ስርዓቱን ለማበልጸግ ዩኒቨርሲቲው በተለይ እስከ ሶስተኛ ዲግሪ ድረስ ትምህርት ከመስጠት ባለፈ የተለያዩ ጥናቶችን በማከናወንና ውጤቶች ለህትማት በማብቃት ለዓለም እንዲደርስ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

ዩኒቨርሲቲው በቅርቡ የሚገኙትን የጉጂና ቦረና የገዳ ሥርዓትን በማጥናትና ትሩፎቶቹ እንዲተዋወቅና ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ የሚያደረገውን ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ገልጸዋል።

የገዳ ሥርዓት እሴቶች የሆኑት ሠላምና አቃፍነት ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፈ በትኩረት እየሰራ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የኦሮሚያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ አቶ ከበደ ዴሲሳ ናቸው።

በተለይ ለሥርዓቱን በቂ ትኩረት በመስጠት በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ተቋም/ዩኒሴኮ/ እንዲመዘገብ ከማድረግ ባለፈ ትውልዱ እሴቶችን በመረዳት እንዲያደግ በትምህርት ስርዓት ውስጥ በማካተት ከ1ኛ ደረጃ ጀምሮ እየተሰጠ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በተለይም ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ሥርዓቱን በቅርበት በማጥናትና ምርምር በማድረግ ለመማር ማስተማር ግብዓት ከማቅረብ ባለፈ ለዓለም ማህበረሰብ ለማስተዋወቅ እያደረገ ያለው ጥረት የሚመሰገን መሆኑን አንስተዋል።

ቢሮው የገዳ ሥርዓትን ለማበልጸግ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቅሰው ትውልዱ በተለይም ወጣቱ ከአዳ ሰንቄዎችና አባ ገዳዎች የገዳ እሴቶችን በመማር ለአካባቢው ሠላም የበኩሉን መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል።

በክብር እንግድነት የተገኙት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሃብታሙ ሲሳይ በበኩላቸው የኦሮሞ ህዝብ ከሺህ ዓመታት በፊት የዓለም የዴሞክራሲ ተምሳሌት በሆነው የገዳ ሥርዓት ሲተዳደር መኖሩን ዓለም በአደባባይ ከመሰከረ አራት ዓመታት እንደሞላው ጠቅሰዋል።

በተለይ የጉጂ ፣የቦረና ፣የኬሪዮና ቱለማ ኦሮሞዎች ጫናዎችን ተቋቁመው ሥርዓቱ ከትውልድ ወደ ትውልድ ተላልፎ ለዛሬ እንዲበቃ ማድረጋቸወን አውስተው የገዳ ሥርዓት ለዛሬ እንዲበቃ ላደረጉ አባ ገዳዎችና አዳ ስንቄዎች ክብር ይገባቸዋል ብለዋል።

የገዳ ስርዓት የዴሞክራሲ ምንጭ ነው ያሉት ሚኒስተር ዴዴታው ጉጂ ለ73ኛ ጊዜ ቦረና ለ71ኛ ጊዜ የሥርዓቱ መሪ የሆነወን አባ ገዳ በሠላማዊ መንገድ መቀየር መቻሉ በቂ ማሳያ መሆኑንም አስረድተዋዋል።

የማይዳሰሱ ቅርሶች ህልውናቸው የሚወሰነው የተለያዩ ጫናዎችን ተቋቁመው ይዘታቸው ሳይሸራርፍ ከትውልድ ወደ ትውልድ መተላለፋቸው እንደሆነ ገልጸዋል።

በዚህ ረገድ በዩኔስኮ ከተመዘገቡ የማይዳሰሱ ቅርሶች አንዱ የሆነው የገዳ ሥርዓት ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ ሁሉም ሃላፊነቱን ሊወጣ አንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም የገዳ ሥርዓትን ጨምሮ ሌሎች ባህላዊ እሴቶች እንዲበለጽጉና እንዲለሙ ሃላፊነቱ እንደሚወጣ አስታውቀዋል።

ሁለት ቀናት በሚቆየው የፓናል ውይይቱ የተለያዩ ጥናታዊ ጹሁፎች ቀርበው ውይይት እየተደረገባቸው ይገኛል።

ከኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች የተወጣጡ አባ ገዳዎችና አዳ ስንቄዎች፣ ከፌደራል እስከ ወረዳ የሚገኙ የመንግስት ሥራ ሃላፊዎች፣ ምሁራንና ተማሪዎች በውይይት መድረኩ በመሳተፍ ላይ እንደሚገኙ ሪፖርተራችን ከሥፍራው ዘግቧል።