የህብረት ስራ ማህበራት ከማህበረሰቡ የሚነሳባቸውን ቅሬታ ለመፍታት አሰራራቸውን እንዲያዘምኑ ተጠየቀ

86

አዲስ አበባ፣ ጥር 1 /2013 ( ኢዜአ) የህብረት ስራ ማህበራት በአገልግሎት አሰጣጣቸው ከማህበረሰቡ የሚነሳባቸውን ቅሬታ ለመፍታት አሰራራቸውን ሊያዘምኑ እንደሚገባ ተጠቆመ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ህብረት ስራ ኤጀንሲ በህብረት ስራ ማህበራት የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል ጥናት ይፋ አድርገዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ንግድ ቢሮ ሃላፊ አቶ አብዱልፈታህ የሱፍ እንደተናገሩት የህብረት ስራ ማህበራት የኑሮ ውድነት በማረጋጋት ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ አላቸው።

የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርት አቅርቦቶችን በተለያዩ ቦታዎች ትስስር በመፍጠር ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብም ከፍተኛ ስራ መስራታቸውን ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ ማህበራቱ አገልግሎት መስጠታቸው እንዳለ ሆኖ በህብረተሰቡ የሚነሱባቸው ቅሬታዎች እንዳሉም ጠቁመዋል።

የምርት አቅርቦት እና መሰረታዊ የሆኑ ምርቶችን ለይቶ ማቅረብ ላይ እንዲሁም ከአሰራር አኳያ ውስንነቶች መኖራቸውን አንስተዋል።

በመሆኑም የህብረት ስራ ማህበራት በአገልግሎት አሰጣጣቸው ከማህበረሰቡ የሚነሳባቸውን ቅሬታ ለመፍታት አሰራራቸውን ሊያዘምኑ ይገባል ብለዋል።

በመሆኑም በህብረት ስራ ማህበራት የሚስተዋሉ ችግሮችን በጥናት በመለየት የመፍትሄ ሃሳቦች መቀመጣቸውን አቶ አብዱል ፈታህ ገልጸዋል።

በዚህም ህብረት ስራ ማህበራት አገልግሎት አሰጣጣቸውን በማዘመን ለህብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት ሊሰጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በተለይም ለብክነት የሚዳረጉ አሰራሮችን መለየት እንዲሁም ብቃት ያላቸው ባለሙያዎችን በመቅጠር ግልጽና ተጠያቂነት ያለው አሰራርን ሊዘረጉ ይገባል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ህብረት ስራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ውብነህ እምሩ በበኩላቸው ህብረት ስራ ማህበራት ምርቶችን በተመጣጠነ ዋጋ ለከተማው ነዋሪ እያቀረቡ መሆኑን ገልጸዋል።

አምራቾችን ለማበረታታት አምራችና ሸማችን ለማገናኘት በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በማህበራት የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የአቅም ግንባታ መድረኮችን ለመፍጠር በዝግጅት ላይ መሆናቸውንም አንስተዋል።

በህገወጥ መንገድ ተሰማርተው የሚገኙ ማሀበራትንም አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃ እየተወሰደባቸው ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም