የዩኒቨርሲቲዎች የምርምር ውጤቶች ለህብረተሰቡ ተደራሽ ሊሆኑ ይገባል - ኢንስቲትዩቱ

98

ድሬዳዋ፣  ጥር 01/2013(ኢዜአ) በየዩኒቨርሲቲዎች የሚከናወኑ የምርምር ውጤቶች ለህብረተሰቡ ተደራሽ በመሆን ችግር እንዲፈቱ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ የፌደራል የፍትህ፣ የህግ ምርምርና ሥልጠና ኢንስቲትዩት አሳሰበ፡፡

የፍትህ ተደራሽነትና የሰብአዊ መብት ጉዳዮች ላይ የተካሄዱ  ጥናቶች የቀረቡበት ሀገር አቀፍ የውይይት መድረክ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ተካሄዷል፡፡

የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘካሪያስ ኢርኮላ በመድረኩ እንደተናገሩት፤ የቀረቡት ጥናቶች በሀገሪቱ የሚስተዋሉ የህግ ከፍተቶች፣ የሚያስፈጽሙ አካላት እና አሰራሮች ላይ የሚታዩ ችግሮችን ያመላከቱ ናቸው።

ጥናቶቹ መደርደሪያ ላይ የሚቀመጡ ሣይሆን የህብረተሰቡን መሠረታዊ ችግሮች ትርጉም ባለው መንገድ እንዲፈቱ ለሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማትና ለፖሊሲ አውጪዎች በመስጠት ተግባራዊነታቸውንም መከታተል ይገባል ብለዋል፡፡

በውይይት የዳበሩትና የተጠናቀቁት የጥናት ውጤቶች ወደ ህግ አውጪውና አስፈጻሚው እንዲደርሱ  መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

መሰል ምርምሮችንና ጥናቶች ከማከናወን ባሻገር የዩኒቨርሲቲዎቹ የጥናት ቡድኖች ወደ ህብረተሰቡ ውስጥ በስፋት ገብተው መስራት ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

አቶ ዘካሪያስ እንዳሉት የሚወጡ ህጎች ጥናትና ምርምርን ተመርኩዘው እንዲዘጋጁ  እንዲሁም ቀደም ሲል የነበሩ ክፍተቶችን ለማስተካከልም  ያግዛሉ፡፡

በተጨማሪም ኢንስቲትዩቱ በጥናቱ ግኝቶቹ የተመላከቱትን  ክፍተቶች በህግ እስኪሻሻሉ ድረስ ለሚመለከተው የፍትህ አካላት ሥልጠና በመስጠት ችግሮቹ በአሰራር እንዲፈቱ ይሰራል ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰብአዊ መብት የሶስተኛ ዓመት ዲግሪ ተማሪ ሆነልኝ ሐይሉ ስለሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሰብአዊ መብት ጥሰቶችና የመፍትሄ ሃሳቦች ላይ ያተኮረ ጥናታዊ ፅሁፍ ለውይይት አቅርበዋል፡፡

ተማሪ ሆነልኝ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በብሔር ተኮርና በፖለቲካ መካረሮች ሣቢያ እየተፈናቀሉ የሚገኙ ዜጎች የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እየተፈፀመባቸው ነው፡፡

እነዚህን ችግሮች ለመከላከል ሀገሪቱ የፈረመችውና የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች መብቶች እንዲከበሩ የሚያስችለውን የካንፓላን ኮንቬንሽን መተግበር  እንደሚገባ አመልክቷል፡፡

ኮንቬንሽኑ ወደ ሥራ ለማስገባት የፖሊሲና የህግ ማዕቀፍ በፍጥነት ሊበጅለት  ይገባል ብሏል፡፡

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር መገርሳ ቃሲም በበኩላቸው፤ የውይይት መድረኩ የሰው ልጆች ሰብአዊ መብቶችና ነጻነቶች እንዲከበሩ የሚያግዙ ገንቢ ሃሳቦች የተንፀባረቁበት እንደነበር ተናግረዋል፡፡

ከውይይቱ ዩኒቨርሲቲው በርካታ ልምዶች ማግኘታቸውን አመልክተው በመሰል ጉዳዮች ላይ ምርምርና ጥናቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥልም ገልጸዋል፡፡

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ  ከኢንስቲትዩቱ ጋር በመተባበር ለሁለት ቀናት ባዘጋጀው መድረክ በፍትህ ተደራሽነት፣ሰብአዊ መብት አያያዝ፣የህግ የበላይነትና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ማዕከል ያደረጉ ከአስር በላይ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው በተሳታፊዎች ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

በሀገሪቱ ከሚገኙ የተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተውጣጡ ምሁራንና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት በውይይት መድረኩ ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም