በምሥራቅ ሐረርጌ በ460 ተፋሰሶች ውስጥ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ለማካሄድ እንቅስቃሴ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በምሥራቅ ሐረርጌ በ460 ተፋሰሶች ውስጥ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ለማካሄድ እንቅስቃሴ ተጀመረ

ሐረር ፤ ጥር 1 ቀን 2013(ኢዜአ) በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን በዘንድሮ በጋ ወራት በ460 ተፋሰሶች ውስጥ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ለማካሄድ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ተጀመረ።
ሥራው በኮንቦልቻ ወረዳ ኤጉ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ዛሬ በተጀመረበት ወቅት የዞኑ ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ሚስኪ መሀመድ እንደተናገሩት በ20 ወረዳዎች ውስጥ ከ177ሺ ሄክታር መሬት በላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች ይከናወናሉ።
በወረዳዎቹ በሚገኙ 460 ተፋሰሶች ውስጥ የሚከናወነው ይሄው ሥራ ለ45 ቀናት እንደሚቆይ አስረድተዋል።
ሃላፊዋ እንዳሉት እርከን ጨምሮ ሌሎችም የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች ላይ ከ700ሺህ በላይ አርሶአደሮች እና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።
የምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አያሌው ታከለ በበኩላቸው ቀደም ብሎ የተከናወነው የተፋሰስ ልማት ስራ አካባቢዎችን ከበረሃማነት ወደ ለምነት እየቀየረ ይገኛል ብለዋል።
በተለይ በዞኑ ጠፍተው የነበሩ ምንጮች በመመለሳቸው አርሶአደሩ እንዲጠቀምባቸው እድል መፈጠሩን አመልክተዋል።
በአሁኑ ወቅትም በየወረዳው ለማከናወን የታቀደውን የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራን ስኬታማ ለማድረግ በጋራ መረባረብ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በኮንቦልቻ ወረዳ የኤጉ ቀበሌ ገበሬ ማህበር አርሶ አደር አብደላ ዩስፍ በሰጡት አስተያየት የልማት ተጠቃሚነታቸውን እያጎለበተ ያለውን የተፋሰስ ልማትን ዘንድሮም ለማጠናከር እየተሳተፉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ባለፉት ዓመታት ባከናወነው የእርከን ሥራ ተራቁተው የነበረ የአካባቢያቸው መሬት ማልማት መቻላቸውን የተናገሩት ደግሞ አርሶአደር መሀመድ ሀሰን ናቸው።
ዘንድሮም በአካባቢያቸው በተጀመረው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ላይ በመሳተፍ ለውጤታማነቱ የድርሻቸውን እንደሚወጡም ገልጸዋል።
በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ባለፈው ዓመት በጋ ወራት በ331 ተፋሰሶች ውስጥ ከ141ሺ ሄክታር መሬት ላይ የተለያዩ የእርከን ስራዎች መከናወናቸው ተመልክቷል።