ክልል አቀፍ የአፋር ወጣቶች ኮንፈረንስ ተጀመረ

1866

ሠመራ፤ ጥር 1/2013(ኢዜአ) “የኢትዮጵያ ሀገረ-መንግስት ግንባታ የወጣቶች ሚናና አለም አቀፍዊ ልምዶች” በሚል መሪ ሃሳብ የተዘጋጀ ክልል አቀፍ የአፋር ወጣቶች ኮንፈረንስ ዛሬ በሠመራ ከተማ ተጀመረ።

ለአንድ ቀን በሚካሄደው  ኮንፍረንስ  ከክልሉ ሁሉም ወረዳዎች የተወጣጡ ከ1ሺህ 500 በላይ ወጣቶች እየተሳተፉ ነው።

የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ሀላፊ አቶ አህመድ ኢብራሂም ኮንፍረንሱ ሲጀመር እንደተናገሩት ወጣቶች የሀገሪቱን ሁሉን አቀፍ ለውጥ  በአግባቡ ተረድተው ለመጠቀም ገንቢ ሚና መጫወት ይኖርባቸዋል።

በተለይም በሀገራዊ ጉዳዮች በባለቤትነት ስሜት በንቃት በመሳተፍ ስህተቶችን በማረምና  መልካሙን በመደገፋ በሀገረ-መንግስት ግንባታ ውስጥ በንቃት መሳተፍ እንደሚኖርባቸው ገልጸዋል።

ለዚህም ያላቸውን አፍላ ጉልበት፣ ክህሎትና አውቀት ከስሜታዊነት በጸዳ መልኩ ምክንያታዊ ሆነው መንቀሳቀስ ከወጣቶች የሚጠበቅ መሆኑንም አብራርተዋል።

የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ኢሴ አደም በበኩላቸው የኮንፍረንሱ ዓላማ  በሀገረ-መንግስት ግንባታ ወጣቶችን ከተመልካችነት ወደ ተሳታፊነት ለማሻገር የሚያግዝ ንቅናቄ ለመፍጠር ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም ብሄራዊና ሀገራዊ ማንነትን አንዱ ሌላውን የሚጋፋ ሳይሆን ሁለቱን አጣጥሞ በማስቀጠል በሀገራዊ አንድነትንና የሰላም እሴት ግንባታ ላይ የጎላ ሚና እንዲኖራቸው  ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር መሆኑን አስረድተዋል።

ወጣቶች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ የሚያጋጥሙ ፈተናዎችና ብዥታዎችን በማጥራት የመፍትሄ አቅጣጫዎች ለመያዝ ተመሳሳይ ኮንፍረንሶች እስከ ታችኛው የአስተዳዳር እርከን እንደሚቀጥል አስታውቀዋል። 

በኮንፍረንሱ በሀገረ-መንግስት ግንባታና  የወጣቶች ሚና ዙሪያ የመነሻ ጽሁፋ ቀርቦ ውይይት እንደሚካሄድበት ይጠበቃል።