በመተከል በዜጎች ላይ ለተፈፀመው ጭፍጨፋ የጉሙዝና የሌሎች ብሄረሰቦች አመራሮችም እጅ አለበት... የድባጤ ወረዳ ነዋሪዎች

130

መተከል፤ ጥር 1/2013(ኢዜአ) በመተከል ዞን በዜጎች ላይ በተፈፀመው ጭፍጨፋና የንብረት ውድመት የጉሙዝና የሌሎች ብሄረሰቦች አመራሮችም እጅ እንዳለበት የድባጤ ወረዳ ነዋሪዎች ተናገሩ።

በፌዴራል መንግስት ተቋቁሞ የመተከል ዞን የጸጥታና ህግ ማስከበር ስራ የተረከበው ኮማንድ ፖስት በዞኑ የተለያዩ ቀበሌዎች መሽጎ በነበረው ሽፍታ ላይ እርምጃውን አጠናክሮ ቀጥሏል።

ኮማንድ ፖስቱ ከመኖሪያ አካባቢዎቻቸው የተፈናቀሉ ወገኖችንም ተመልሶ ማቋቋምና ዘላቂ ሰላም ማግኘት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ከህብረተሰቡ ጋር ውይይት በማድረግ ላይ ይገኛል።

የኮማንድ ፖስቱን የጸጥታና ህግ ማስከበር ስራ የሚመሩት ሌተናል ጀነራል አስራት ዴኔሮ እና የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክትል ፕሬዘዳንት ጌታሁን አብዲሳ ከድባጤ ወረዳ ነዋሪዎች ጋር ውይይት አድርገዋል።

የውይየቱ ተሳታፊዎች እንዳሉት፤ በወረዳው ብሎም በዞኑ ለተፈጸመው ዘርን መሰረተ ያደረገ ጥቃትና ውድመት ከጉሙዝም ሆነ ከሌሎች ማህበረሰቦች የተወከሉ አመራሮች ተጠያቂ ናቸው።

በመሆኑም በዚህ ወንጀል ተሳታፊ የሆኑ ሁሉ በህግ እንዲጠየቁ ነዋሪዎቹ ጥያቄ አቅርበዋል።

የዚህ ሁሉ እልቂትና ጭፍጨፋ መሪና አቀናባሪ የህወሃት ቡድን ያቋቋመው የጉሙዝ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉህዴን) ነው የሚሉት ተሳታፊዎቹ፤ ከጉሙዝ ወጣቶች በማታለል ለጥፋት እየመለመለ መሆኑንም ገልጸዋል።

የጉህዴንን ውሳኔ አንቀበልም ያሉ የጉሙዝ ማህበረሰብ አባላትም እንግልት ከማድረስ አልፎ ግዲያ እንዲፈፀምባቸው እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ብልጽግ ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ኢሳቅ አብዱልቃድር በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚኖር ማንኛውም ማህበረሰብ በሰላምና በነፃነት የመኖር መብት አለው ብለዋል።

ዘረኛውን የህወሃት ቡድን በመታገል የመጣውን ለውጥ ብልጽግና ለሁሉም የምትመች አገር ለመገንባት እየሰራ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

የኮማንድ ፖስቱን የጸጥታና ህግ ማስከበር ስራው የሚመሩት ሌተናል ጀነራል አስራት ዴኔሮ በዞኑ አስተማማኝና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ኮማንድ ፖስቱ በሽፈታዎች ላይ ጠንካራ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን እርምጃ መውሰድ ብቸኛ አማራጭ ባለመሆኑ የጉሙዝ አባቶች በተሳሳተ መረጃ ወይም በፍርሃት ጫካ የገቡ ዜጎች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

በርካታ ታጣቂዎችም በሰላማዊ መንገድ እጃቸውን እየሰጡ መሆኑንም ገልጸዋል።

ኮማንድ ፖስቱ "በዞኑ አስተማማኝ ሰላም ሳያሰፍንና ወንጀለኞችን ለህግ ሳያቀርብ የትም አይሄድም" ያሉት ሌተናል ጀነራል አስራት፤ ከቀበሌ እስከ ወረዳ ያሉ አመራሮች በህዝብ የተመረጡ ይሆናሉም ብለዋል።

የወንጀል ተሳታፊ የነበሩ ሰዎች በሃላፊነት እንዳይካተቱ ከህብረተሰቡ ጋር ሆነን የማጥራት ስራ እናከናውናለን ሲሉም ሌተናል ጀነራል አስራት አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም