በሐረሪ ክልል ከ105 ሚሊየን ብር በሚበልጥ ወጪ የአስፓልት መንገድ ግንባታ እየተካሄደ ነው

1619

ሐረር ፤ጥር 1/ 2013(ኢዜአ) በሐረሪ ክልል ከተማና ገጠር ቀበሌዎች ከ105 ሚሊየን ብር በሚበልጥ ወጪ የአስፓልት መንገድ ፕሮጀክት ግንባታ በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ገለጸ። 

የቢሮው ሃላፊ አቶ ፈርሃን ዚያድ እንደገለጹት በክልሉ በተያዘው የበጀት ዓመት እየተካሄደ ያለው የአስፓልት መንገድ ከ14 ኪሎ ሜትር በላይ የሚሸፍን ነው።

በከተማና ገጠር ቀበሌዎች  ለሚካሄደው  ለዚሁ መንገድ ግንባታ ማስፈጸሚያ  ከ105 ሚሊየን ብር በላይ  መመደቡን አስታውቀዋል።

ከመንገድ ፕሮጀክቱ ውስጥ  በሸንኮር ወረዳ ከደሴ ሆቴል እስከ ምሰራቅ ካፌ  የሚሸፍነው የ1 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር አስፓልት የካሳ ክፍያና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች  በማስፈጸም  ወደ ግንባታ የተገባው ይገኝበታል።

ሌላው ከአው አብዳል እስከ ኤረር ቀበሌ ገበሬ ማህበር እየተገነባ የሚገኘው የ13 ኪሎ ሜትር የቁፋሮና የመሬት ጠረጋ ስራው   መጠናቀቁን አስረድተዋል።

የአስፓልት መንገድ ግንባታውን  በተያዘለት እቅድ መሠረት  በበጀት ዓመቱ  መጨረሻ አጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት በትኩረት  እየተሰራ ይገኛል ብለዋል::

የመንገዱ መገንባት ህብረተሰቡም ከዚህ ቀደም  ሲነሳ  የነበረው የመሰረተ ልማት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እንደሚያግዝ  የቢሮው ሃላፊ ገልጸዋል።

የእግረኛ መንገድ ጨምሮ 15 ሜትር የጎን ስፋት ያለው የአስፓልት መንገዱ ግንባታ በአካባቢው ከመንገድ ጥበት ጋር ተያይዞ ይከሰት የነበሩ የትራፊቅ መጨናነቅና አደጋን ለማስቀረት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አመልክተዋል።

ህብረተሰቡም ለፕሮጀክቱ ግንባታ ስኬታማነት  እያሳየ ላለው ትብብርና ድጋፍ ሃላፊው አመስግነዋል።

ከሸንኮር ወረዳ ነዋሪዎች መካከል አቶ ሳሙኤል ግርማ በሰጡት አስተያየት የአስፓልት መንገዱ ግንባታ ህብረተሰቡ ከዚህ ቀደም ሲጠይቅ የነበረው የመሰረተ ልማት ጥያቄ ምላሽ የሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

የመንገዱ መገንባት  የትራፊክ መጨናነቅና  አደጋን ለመቀነስ የሚያግዝ በመሆኑ ህብረተሰቡ ለሥራው መሳካት  እያደረገ ያለውን ትብብርና ድጋፍ መቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል።

በመንገዱ  ጥበት ምክንያት በተለይ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ሲሄዱና ሲመለሱ ለትራፊክ አደጋ ሲጋለጡ መቆየታቸውን የገለጹት ደግሞ ሌላው የአካባቢው ነዋሪ  አቶ ታለለጌታ ባሳዝነው ናቸው።

በአሁኑ ወቅት የሚገነባው የአስፓልት መንገድ ችግሩን ያቃልላል ብለው እንደሚጠብቁ ገልጸው በሥራውም ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።