የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከመተከል ዞን ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ አደረገ

2122

ጎንደር፣ ጥር 1/2013( ኢዜአ ) ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በቤንሻጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ግምታቸው አንድ ሚሊዮን ብር የሚጠጋ የምግብ፣ የአልባሳትና የቤት መገልገያ ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን አስታወቀ።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር አስራት አጸደወይን ለኢዜአ እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው በትናንትናው እለት ቁሳቁሶቹን ወደ አካባቢው በማጓጓዝ ለተፈናቀሉ ወገኖች እንዲደርስ ለሚመለከተው አካል አስረክቧል።

ዩኒቨርሲቲው ካደረጋቸው ድጋፎች መካከልም 191 የስፖንጅ ፍራሾች፤ 600 አልባሳትና ለቀለብ የሚውሉ 138 ኩንታል ጤፍ፣ ማሽላ፣ ቦለቄ፣ ሽንብራ እንዲሁም 5 ኩንታል የዳቦ ዱቄት ይገኝበታል፡፡ 

በተጨማሪም አንድ ሺህ 498 የመመገቢያ የመጠጫና የማብሰያ ቁሳቁሶችን ዩኒቨርሲቲው ለተፈናቃዮቹ እንዲደርስ መላኩን ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰባዊ አገልግሎቱን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ከማድረግ አኳያ ባለፉት አመታት በርካታ ሰብአዊ ድጋፎችን ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰዋል።

በቅርብ ካደረጋቸው ድጋፎች መካከልም በጣና ሃይቅ ሙላት የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ በማቋቋም እንዲሁም በምስራቅ አማራ የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተደረገው ጥረት ላይም መሳተፉ ተገልጿል።