የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ28 ሺህ በላይ ወጣቶችን ስራ አስጀመረ

98

አዲስ አበባ፣ ጥር 1 /2013 ( ኢዜአ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተቀናጀ የከተማ ውበት፣ የአረንጓዴ ልማት፣ ደረቅ ቆሻሻ አሰባሰብና ሌሎች ዘርፎች የስራ ዕድል የተፈጠረላቸውን ከ28 ሺህ በላይ ወጣቶችን በዛሬው እለት ስራ አስጀመረ።

የስራ እድል የተፈጠረላቸው ወጣቶች ለሁለት ሳምንታት በተለያዩ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ስልጠና ወስደው ያጠናቀቁ መሆኑም ተገልጿል።

የከተማ አስተዳደሩ ጽዱ፣ ውብና አረንጓዴ ከተማን የመፍጠር እቅዱ ከስራ እድል ፈጠራ ጋር አቀናጅቶ ለመፈጸም መሆኑ ተጠቅሷል።

ለስራ እድል ፈጠራው የከተማ አስተዳደሩ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ መመደቡም ታውቋል።

ከ28 ሺህ 162 የስራ ዕድሉ ተጠቃሚ ወጣቶች መካከል 53 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው።

በዛሬው እለት በተካሄደው የስራ ማስጀመሪያ መርሓ ግብር የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ የስራ ስምሪት በመስጠት አስጀምረዋል።

የ23 አመት ወጣት የሆነው ዋቁማ መዝገቡ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋም የመጀመሪያ ዲግሪውን በጂኦግራፊ የሙያ መስክ ቢያገኝም እንዳሰበው በፍጥት ስራ እንዳላገኘ ይናገራል።

ከተማ አስተዳደሩ የስራ እድል ከፈጠረላቸው ወጣቶች መካከል አንዱ መሆኑ ሰርቶ እራሱንና አገሩን ለመጥቀም እንደሚጥርም ገልጿል።

ወጣት ሃያት ጠቢም እና ተስፋነሽ ባዳርጋ ከስራ አጥነት ወደ ስራ ባለቤትነት መሸጋገራቸው ሰርተው ለመለወጥ ተስፋ እንዲሰንቁ አድርጓቸዋል።

ለስራ የሚያግዛቸውን ስልጠና መውሰዳቸውን ገልጸው በተፈጠረላቸውን የስራ እድል ሰርተው ለመለወጥ  መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ ስራ የተፈጠረላቸው ወጣት ሴትና ወንዶች የተሰጣቸውን እድል በመጠቀም ለሌሎች በአራአያነት አሻራቸውን የሚያስቀምጡ እንዲሆኑ መክረዋል።

ወጣቶቹ በትጋት ሰርተው የከተማዋን ገጽታና ራሳቸውን እንዲለውጡም ምክትል ከንቲባዋ ጠይቀዋል።

አገርን ለመለወጥ መንግስት የሚፈጥራቸውን የስራ እድሎች ዜጎች በአግባቡ በመጠቀም በትብብር መስራት እንዳለባቸውም ተናግረዋል።

ወጣቶች ውጤታማ እንዲሆኑ በከተማ አስተዳደሩ ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግ ገልጸው ፈጻሚ አካላት በዚህ ዙሪያ ሃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡም አሳስበዋል።

የስራ እድል የተፈጠረላቸው ወጣቶች ከከተማዋ ከሁሉም ክፍለ ከተሞች ግልጽ በሆነ መስፈርት እንዲሳተፉ መደረጉንም አስረድተዋል።

የስራ እድል ልየታው ባለፉት ጊዜ ይነሱ የነበሩ የተጠቃሚነትን ቅሬታዎች በሚፈታ መልኩ የተከናወነ መሆኑንም አብራርተዋል።

በዚህም ዜጎች በቀበሌያቸው፣ በወረዳና ክፍለ ከተማ ባሉ የስራ እድሎች ቅድሚያ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል ብለዋል።

ስራ የተፈጠረላቸውን ወጣቶች የማደራጀትና ቦታ የማስረከብ ስራ እየተከናወነ ሲሆን በዛሬው እለት ለ616 ኢንተርፕራይዞች የመስሪያ ቁሳቁስና የቦታ ርክክብ ተደርጓል።

ከቀጣይ ሰኞ ጀምሮ ደግሞ ለ1 ሺህ 754 ኢንተርፕራይዞች ርክክብ ይደረጋል ተብሏል።

በተመሳሳይ በዚህ መርሃ ግብር ከተማ አስተዳደሩ የጎዳና ተዳዳሪዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም እየሰራ መሆኑን ምክትል ከንቲባዋ ገልጸዋል።

በዚህም 4 ሺህ የሚሆኑትን በማሰልጠን ወደ ስራ ለማስገባት ዝግጅት መደረጉ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም