ዳያስፖራው በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ለተቸገሩ ወገኖችና ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አድርጓል …የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ

1732

አዲስ አበባ፣ ጥር 1 /2013 (ኢዜአ) ዳያስፖራው በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ለተቸገሩ ወገኖችና ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ በገንዘብና በአይነት ድጋፍ ማድረጉን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ አስታወቀ።

ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታም በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት 76 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉ ተገልጿል።

የሕወሓት የጥፋት ቡድን በአገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ ያደረሰውን ጥቃት ተከትሎ መንግስት በትግራይ ክልል የሕግ ማስከበር እርምጃ መውሰዱ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት ለኢዜአ እንደገለጹት በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ለተቸገሩ ወገኖችና ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ድጋፍ የሚያሰባስብ ብሔራዊ ኮሚቴ መቋቁሙንና በኤጀንሲው የሚመራ የዳያስፖራውን ድጋፍ የሚያስተባብር ንዑስ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን ገልጸዋል።

በሃብት ማሰባሰብ ስራው እስካሁን ዳያስፖራው ሰብአዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖችና ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ በገንዘብና በአይነት ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።

የአይነት ድጋፍ በተለይም ከሕክምና ቁሳቁስና መሳሪያዎች አንጻር የሚያስፈልጉ ድጋፎች በጤና ሚኒስቴር አማካኝነት በመለየት ወደ አገር ቤት እንዲላኩ ተደርጓልም ብለዋል።

ዳያስፖራው በአጭር ጊዜ ውስጥ የቀረበለትን ጥሪ ተቀብሎ ያደረገው ድጋፍ የሚደነቅና አገር ወዳድነቱን በተግባር ያሳየበት መሆኑንም ዳይሬክተሯ ገልጸዋል።

ከድጋፉ በተጨማሪ መንግስት በትግራይ ክልል ያደረገውን ሕግ ማስከበር እርምጃ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲኖረው የማድረግ ስራ ተከናውኗል ብለዋል።

በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ለሚገኙ የስራ ሃላፊዎችና ዲፕሎማቶች ማብሪሪያ በመስጠት የዳያስፖራው ማህበረሰብ የበኩሉን አስተዋፆ ማድረጉንም አስታውሰዋል።

የጋራ መግለጫ በማውጣት፣ ሀሰተኛ ትርክቶችን በማጋለጥና ህግ የማስከበር እርምጃውን በመደገፍ ሰልፍ በማድረግ ለሀገራቸው ያላቸውን አጋርነት መግለጻቸውን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ዳያስፖራው በ2013 ዓ.ም በጀት ዓመት ስድስት ወራት ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ 76 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉንም ዋና ዳይሬክተሯ ጠቁመዋል።

ከተደረገው የገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ ዳያስፖራው በሕዳሴ ግድብ ላይ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ትክክለኛ መረጃ ተደራሽ እያደረጉ እንደሆነ ተናግረዋል።

የበይነ መረብ የምክክር መድረኮችን በማዘጋጀት፣ በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በመቅረብና የማህበራዊ ትስስር ገጾችን በመጠቀም ዳያስፖራው በሕዳሴው ግድብ ጠንካራ የሚባል የሕዝብ ግንኙነት ስራ እያከናወነ ነው ብለዋል።

በ2013 ዓ.ም በጀት ከዳያስፖራው ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ 200 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱንም ጠቁመዋል።

ዳያስፖራው በ2013 ዓ.ም በጀት ዓመት ስድስት ወራት በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመከላከልና ለመቆጣጠር ለሚከናወነው ስራም ከ208 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብና የአይነት ድጋፍ ማድረጉን ነው ወይዘሮ ሰላማዊት ያስረዱት።

በተለይም ዳያስፖራው ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሕክምና የሚያስፈልጉ የሕክምና ቁሳቁሶችና መሳሪያዎች ገዝተው ወደ አገር ቤት መላካቸውን አመልክተዋል።

በተጨማሪም በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጰያዊያን የህክምና ባለሙያዎች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

የጤና ባለሙያዎችና ተመራማሪዎች የበይነ መረብ ምክክር መድረኮችን በማዘጋጀት ለመንግስት ወረርሽኙን መከላከል የሚያስችሉ ሳይንሳዊ ምክረ ሀሳቦችን እያቀረበ እንደሆነ አስረድተዋል።

ለገበታ ለአገር ፕሮጀክትም እስካሁን ዳያስፖራው ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል።

በ2013 ዓ.ም ኤጀንሲው ከዳያስፖራው ለገበታ ለአገር ፕሮጀክት 50 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ማቀዱንምተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ለሚከናወኑ የልማት ስራዎች ዳያስፖራው በገንዘብና በእውቀቱ እያደረገ ያለው ድጋፍ ታሪካዊ የሚባል ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።