የ2013 ቶታል ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድር ዝግጅት ተጠናቋል

70

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 30/2013 ( ኢዜአ) በመጪው እሁድ ለሚካሄደው የ2013 ቶታል ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድር የዝግጅት ሥራ መጠናቀቁ ተገለጸ።

20ኛው የቶታል ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድር የፊታችን እሁድ በአዲስ አበባ ይካሄዳል።

የኮቪድ-19 ቅድመ ጥንቃቄዎችን ታሳቢ በማድረግ ጥር 2 ቀን 2013 ዓ.ም የሚካሄደው 20ኛው ቶታል ታላቁ ሩጫ 12 ሺህ 500 ተሳታፊዎች ብቻ እንደሚኖሩት ታውቋል።

ውድድሩ መነሻውን መስቀል አደባባይ፤ መድረሻው ደግሞ አትላስ አካባቢ እንደሚሆን የገለጸው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የዝግጅት ሥራው መጠናቀቁንም አስታውቋል።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሀብታሙ ሲሳይ እንዳሉት አገራት ስፖርትን ለአገራቸው ልማትና ሁለንተናዊ እድገት እንደ አንድ መሳሪያ ይጠቀሙበታል።

በኢትዮጵያም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ በብሔራዊ ስፖርት ምክር ቤት ሥራ ላይ እንዲውል በተወሰነው አገራዊ የስፖርት ሪፎርም ፕሮግራም ስፖርትን ጤናማና ንቁ ዜጋ ለመፍጠር እንደ አንድ አይነተኛ መሳሪያ መጠቀም እንደሚገባ በግልጽ መቀመጡን ነው ያስረዱት።

"ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ለአገር ገጽታ ግንባታ ብሎም ለቱሪዝም መስፋፋት ትልቅ ሚና ያለው ከመሆኑ ባሻገር የኢትዮጵያዊያን አንድነት፣ ፍቅርና ሰላም መገለጫ ሆኗል" ሲሉም ተናግረዋል።

የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ መስራች እና የቦርድ ሊቀመንበር አትሌት ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ በበኩሉ፤ "ታላቁ ሩጫ በዓለም ላይ አንጋፋ ከሚባሉ የጎዳና ውድድሮች አንዱ ሲሆን ዘንድሮ 20ኛ ዓመቱ ላይ ደርሷል" ብሏል።

በእስካሁኑ የ20 ዓመት የውድድር ጉዞው የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላትም ምስጋናውን አቅርቧል።

የዘንድሮ ውድድር ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ በከፍተኛ ጥንቃቄ የሚደረግ መሆኑንም ገልጿል።

በዘንድሮ ውድድር ከጤና ሯጮች በተጨማሪ 300 የሚሆኑ ወንድ እና ሴት አትሌቶች የሚወዳደሩ ሲሆን አሸናፊ ለሚሆነው አትሌትም የ100 ሺህ ብር ሽልማት እንደሚሰጥ ተገልጿል።

በተጨማሪም የጃፓን፣ ፊንላንድ፣ ፖላንድ እና ቱርክ አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶችም የውድድሩ ተሳታፊዎች እንደሚሆኑ ነው የተገለጸው።

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በአጠቃላይ በ20 ዓመት የውድድር ጉዞው ከ500 ሺህ በላይ ተሳታፊዎችን አስተናግዷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም